ቀጥታ፡

ቀኑ ህብረ ብሔራዊ አብሮነት የሚጠናከርበትና ባህላዊ ትውፊቶች በአደባባይ የሚገለጡበት ነው

ሆሳዕና፤ ህዳር 26/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህብረ ብሔራዊ አብሮነት የሚጠናከርበትና ባህላዊ ትውፊቶች በአደባባይ የሚገለጡበት መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ገለፁ፡፡

በ20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለመታደም ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የባህል ኪነት ቡድኖች በሆሳዕና ከተማ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡


 

በመርሃ ግብሩ በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ፣ ቀኑ ህብረ ብሔራዊ አብሮነት የሚጠናከርበትና እምቅ ባህላዊ ትውፊቶች በአደባባይ የሚገለጡበት መሆኑን ገልፀዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም በብዝሃነት የደመቀ የአብሮነት ማሳያ መሆኑን በመጠቆም ታዳሚዎች በቆይታቸው እነዚህን እሴቶች በመጋራት መልካምና በደስታ የተሞላ ቆይታ እንዲኖራቸው ተመኝተዋል።

በቆይታቸው በዓሉን ከማክበር ባለፈ በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በመጎብኘት እንዲያሳልፉ ጋብዘዋል።


 

የክልሉ፣ የሀድያ ዞንና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች በስፍራው በመገኘት እንግዶቹን ተቀብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም