የዓድዋ ድል የአፍሪካዊያን የነጻነት ተምሳሌት እና የፓን አፍሪካኒዝም መሠረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የአፍሪካዊያን የነጻነት ተምሳሌት እና የፓን አፍሪካኒዝም መሠረት ነው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 26/2018(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል የአፍሪካዊያን የነጻነት ተምሳሌት እና የፓን አፍሪካኒዝም መሠረት መሆኑን ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡
ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች የዓድዋን ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል፡፡
የሚዲያ ባለሙያዎቹም በጉብኝቱ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ታሪካዊ ክብር፣ የአፍሪካን የነጻነት ተምሳሌት እና የፓን አፍሪካኒዝም መሠረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከቶጎ የመጣችው ጋዜጠኛ ያይቪ ኢቃቤፔ ፊያንዮ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያን በመጎብኘቷ የተሰማትን ደስታ ገልጻ፤ ድሉ ለአፍሪካዊያን የጥንካሬ መሠረት መሆኑንም ተናግራለች፡፡
የዓድዋ ድል ከድል በላይ ትርጉም ያለው የአህጉሪቷ የማንነት መሠረት መሆኑን ጠቅሳ፤ ድሉ የመላ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ነው ብላለች።
የዓድዋ ድል መታሰቢያም ይህን ትልቅ ታሪክ በውስጡ የያዘ መሆኑንም ጠቅሳለች፡፡
ከጋምቢያ የመጣው አብዱላሂ ሴይ በበኩሉ፤ የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን የጀርባ አጥንት መሆኑን ጠቅሶ፤ መታሰቢያው ታሪክን የምንማርበት ድንቅ ቦታ ነው ሲል ተናግሯል፡፡
የሚዲያ ባለሙያዎች የአፍሪካዊያን የድል ታሪክ የሆነውን ዓድዋን ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግሯል፡፡
የዓድዋ ድል ከድል በላይ የሆነ አሸናፊነት የተመዘገበበት መሆኑን አንስቶ፤ ይህም አፍሪካዊያን ሲተባበሩ ታሪክ መሥራት እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
ጉብኝቱ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ወንድማማችነት እና የጋራ የትስስር ታሪክ ይበልጥ እንደሚጠያናክርም ተጠቁሟል፡፡