ኢትዮጵያ አንድነትን፣ ነፃነትን እና ለፍትሕ መታገልን ትወክላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አንድነትን፣ ነፃነትን እና ለፍትሕ መታገልን ትወክላለች
አዲስ አበባ፤ሕዳር 26/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አንድነትን፣ ነፃነትን፣ ለፍትሕ መታገልን የምትወክል በዓድዋ ድል በመንሳት የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል የጀመረች ናት ሲሉ ለፓን አፍሪካ ንቅናቄና ለአፍሪካ ህብረት ምስረታ ጉልህ አበርክቶ ያደረጉ የአፍሪካ መሪዎች ልጆችና የልጅ ልጆች ገለጹ።
አባቶቻችን የቅኝ ግዛትን ታግለው ያገኙትን ፖለቲካዊ ነጻነት በኢኮኖሚው መስክም ልንደግመው ይገባል ብለዋል።
ለፓን አፍሪካ ንቅናቄና ለአፍሪካ ህብረት ምስረታ ጉልህ አበርክቶ ያደረጉ የአፍሪካ መሪዎች ልጆችና የልጅ ልጆች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው አጠቃላይ በሙዚየሙ ባሉ ቅርሶች ዙሪያ ገለጻ እና ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል።
በጉብኝቱ ላይ የመጀመሪያው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የፓትሪስ ሉሙምባ ልጅ፣ የመጀመሪያው የጋና ፕሬዝዳንት ኩዋሜ ኑኩሩማህ ሴት ልጅና የልጅ ልጅ፣ የመጀመሪያው የዛምቢያ ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳ ልጅ፣ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅ እና የታንዛኒያ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ ልጅ ተሳትፈዋል።
በተጨማሪም ታዋቂው ደቡብ አፍሪካዊ ፀረ አፓርታይድ ታጋይ ስቲቭ ቢኮ ልጅ፣ የፀረ አፓርታይድ ታጋይና ሚኒስትር የነበሩት ደቡብ አፍሪካዊ ዋልተር ሲሱሉ ሴት ልጅ፣ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ(ANC) ፕሬዝዳንት፣ የፀረ አፓርታይድ ፖለቲከኛና አክቲቪስት ኦሊቨር ታምቦ ሴት ልጅ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።
የኬኔት ካውንዳ ስድስተኛ ልጅ ካዋቼ ካውንዳ አባቶቻችን አፍሪካን ለማዋሀድ አልመው አልፈዋል ብለዋል።
ይህንን ህልም አሁን ያለው ትውልድ ካልተገበረው ህልሙ ከነርሱ ጋር እንደሚሞት ገልጸው፤ አባቶች ለዚህ በለኮሱት የነጻነት ችቦ ሀገራቸውን ከቅኝ ግዛት ነጥቀው ማውጣት መቻላቸውን ተናግረዋል።
አባቶቻችን የቅኝ ግዛትን ታግለው ያገኙትን ፖለቲካዊ ነጻነት በኢኮኖሚው መስክም ልንደግመው ይገባል ያሉት ካዋቼ ካውንዳ፤ አፍሪካ ብዙ ሀብት በእጇ እያላት ወደ ሌላ የምታይበት ምክንያት ሊኖር እንደማይገባ አመልክተዋል።
የፓትሪስ ሉሙምባ ልጅ ሮናልድ ሉሙምባ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ጦርነት የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል መጀመርያ ነው ብለዋል።
እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት መጀመሪያ እንደሆነ ለልጆች ማስተማር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በጉብኝታቸው መደሰታቸውን ገልጸው አፍሪካውያን በሙሉ ሊጎበኙት የሚገባ ሙዝየም መሆኑን ተናግረዋል።
የጁሊየስ ኔሬሬ ልጅ ማዳራካ ኔሬሬ ዓድዋ የኢትዮጵያ ታሪክ አካል መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ያደረጉት ትግል የፓን አፍሪካኒዝም ዓላማ ቀጣይነትን ያሳየ እንደሆነ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ አንድነትን፣ ነፃነትን፣ ለፍትሕ መታገልን ትወክላለች ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ሌጋሲ ፋውንዴሽን ዋና ጸሀፊ ሙሳ ኢብራሂም ጋዳፊ ናቸው።
ወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች እና ወንዶች ንቁ፣ በተስፋና በሕልም የተሞሉ እንደሆኑ ማስተዋል መቻላቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የነፃነት ታሪክ ከአህጉሪቱ ሌላ ክፍል ካለው የነፃነት ታሪክ ጋር ለማገናኘት ትልቅ ፍላጎት እንዳላቸውም ነው የገለጹት።