የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ-ነገር ይዘት ሰንጠረዥ ለህብረተሰብ ጤናና ለህክምና አገልግሎት እንደመመሪያ የሚያገለግል ሰነድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ-ነገር ይዘት ሰንጠረዥ ለህብረተሰብ ጤናና ለህክምና አገልግሎት እንደመመሪያ የሚያገለግል ሰነድ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 26/2018(ኢዜአ)፦የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ-ነገር ይዘት ሰንጠረዥ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን ለመገንባት፣ ለህብረተሰብ ጤናና ለህክምና አገልግሎት እንደመመሪያ የሚያገለግል ሰነድ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ ገለፁ።
የባህላዊና ዘመናዊ ምግቦችን አዘገጃጀትና የንጥረ-ነገር ይዘት የያዘ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ-ነገር ይዘት ሰንጠረዥ መፅሀፍና የንጥረ-ነገር መረጃ ቋት ይፋ ሆኗል።
የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ-ነገር ይዘት ሰንጠረዥ መፅሀፍና የንጥረ-ነገር መረጃ ቋት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከዓለም የምግብ ድርጅትና ከኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ በስነ-ምግብና ንጥረ-ምግብ ላይ ያተኮሩ የምርምር ስራዎችን ያካሂዳል።
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ-ነገር ይዘት ሰንጠረዥ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ይዘት በሳይንሳዊ ዘዴና ላቦራቶሪ ተተንትኖ ለተጠቃሚ ማድረስ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ-ነገር ይዘት ሰንጠረዥ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን ለመገንባትና በጤናና ትምህርት ተቋማት የምግብ ስርዓት ምክር ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ-ነገር ይዘት ሰንጠረዥ መፅሀፍና የንጥረ-ነገር መረጃ ቋት 726 የምግብ ዓይነትና 69 የምግብ ንጥረ-ነገር ትንተና መረጃን የያዘ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የህብረተሰብ ጤናና ለህክምና አገልግሎት እንደመመሪያ የሚያገለግል እንዲሁም ለተመራማሪዎች ሳይንሳዊ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
በኢንስቲትዩቱ በስርዓተ-ምግብ፣ አካባቢ ጤናና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዳይሬክቶሬት የስርዓተ ምግብና ምግብ ሳይንስ አስተባባሪ ዶክተር እንዳለ አማረ፤ ሰነዱ ህብረተሰቡ የሚመገባቸው ምግቦች ያላቸውን ንጥረ-ነገር ይዘት የያዘ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው ሰነድ ከ20 ዓመት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተሻሻለው ሰነድ የግብርናና የምግብ አዘገጃጀት ሁኔታዎችን መለዋወጥ ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
እያንዳንዱ ሰው በየቀኑ መውሰድ ያለበት የንጥረ-ነገር መጠን እንዳለ አንስተው፤ የተሻሻለው ሰነድ ህብረተሰቡ ተገቢውን የአመጋገብ ስርዓት እንዲከተል ከማድረግ ባለፈ ለተለያዩ ዘርፎች ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል።