የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ ቀጣናዊ የጋራ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ ቀጣናዊ የጋራ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር የጋራ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማሳለጥ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳለጫና ቀጣናዊ የጂኦ-ፖለቲካ ሰላምና ደኅንነትን የማስጠበቅ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ከ120 ሚሊየን በላይ የህዝብ ብዛት ያላት የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ-ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ በሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል የዲፕሎማሲ መርህ በዓለም አቀፍ ሕግጋት መነሻነት ለመደራደር ጭምር ቁርጠኝነቷን በተደጋጋሚ እያስረዳች ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት በሴራ ያጣችውን የባሕር በር ምላሽ ለማስገኘት የሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ጥላሁን ተፈራ(ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በተፈጸመባት ታሪካዊ በደል ከባሕር በር ባለቤትነት እንድትገለል መደረጉን አስታውሰዋል።
በዚህም ምሁራን፣ ዲፕሎማቶች፣ የመገናኛ ብዙኅን ሙያተኞችና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ማስገንዘብ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
የባሕር በር ባለቤትነት የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው ያሉት ምሁሩ፤ በቀጣይም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ለማስገኘት የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ጂኦ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያታዊነት ላይ ተከታታይ ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትም ባላት ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅምና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ቀጣናዊ ዕድገትን በማሳለጥ ሰላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ተመራማሪ ጋሻው አይፈራም(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት በውስጥ ድክመትና በውጭ ተፅዕኖ የተፈጸመ ኢ-ፍትሕዊ በደል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ የጂኦ-ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሰላምና ደኅንነት ትብብርን የማሳለጥ የታሪክ ስብራትን የመጠገን ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።