የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ ነገር ይዘት ሰንጠረዥ የዜጎችን የሥርዓተ ምግብ ደኅንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ ነገር ይዘት ሰንጠረዥ የዜጎችን የሥርዓተ ምግብ ደኅንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 26/2018(ኢዜአ)፦የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግብ ንጥረ ነገር ይዘት ሰንጠረዥ የተደራጀ መረጃን በማቅረብ የዜጎችን የሥርዓተ ምግብ ደኅንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ እገዛ እንደሚያደርግ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለፁ።
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የባህላዊና ዘመናዊ ምግቦች አዘገጃጀት እና የንጥረ ነገር ይዘት የምግብ ሰንጠረዥ መጽሐፍ እና የንጥረ ነገር ቋት ዛሬ ይፋ መሆኑን ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (ፒኦኤ) ዘግቧል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ የቀድሞ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የአዳም ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሊቀ መንበር ደመቀ መኮንን እና ተጋባዥ እንግዶች በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚህ ወቅት፤ የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ስኬት በንጥረ ነገር የበለጸገ የሰብል ምርታማነትን እያሳደገ ነው ብለዋል።
በስንዴና በሌማት ትሩፋት የግብርና ምርታማነት መርሃ ግብር የዜጎችን በንጥረ ነገር የበለጸገ የምግብ አቅርቦት በማሻሻል ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምግቦች አዘገጃጀትና ንጥረ ነገር ይዘት ሰንጠረዥም በትምህርት፣ በሥነ-ምግብና በጤና ዘርፍ ፖሊሲዎችና የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግብዓት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የቀድሞ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የአዳም ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሊቀ መንበር ደመቀ መኮንን፤ የምግብ ዝግጅትና ንጥረ ነገር ሰንጠረዥ መጽሐፍ ምርትና አመጋገብን የሚመራ ሀገራዊ ሰነድ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የምግብ ዝግጅትና ንጥረ ነገር ይዘት ሰንጠረዥ የተደራጀ የሥርዓተ-ምግብ አቅጣጫን በሳይንሳዊ መንገድ የሚያስረዳ መጽሐፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታገሱ ደሳለኝ (ዶ/ር)፤ ዜጎች የምግብ ንጥረ ነገር ይዘቶችን በቀላሉ መገንዘብ በሚያስችላቸው አግባብ መጽሐፉ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የዓለም ምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ፤ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በንጥረ ነገር የበለጸገ የግብርና ምርታማነትን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።