ረቂቅ አዋጁ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስራዎችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
ረቂቅ አዋጁ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስራዎችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 26/2018(ኢዜአ)፦የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ አዋጅ የሀገሪቱን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስራዎች የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ ገለጹ።
በሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት እና የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይፋዊ ውይይት መድረክ አካሂደዋል።
በምክር ቤቱ የፕላን በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ በዚሁ ወቅት፤ የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ በተለያዩ አሰራሮች ላይ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ አንድ ወጥ በሆነ አሰራር፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና ሀገሪቱ ከደረሰችበት ደረጃ ጋር በተጣጣመ መልኩ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሀገሪቱን የበለጸገ የስነ ምህዳር ሀብት ዘላቂ በሆነ ወጥ አሰራር ለማጠናከር የአገልግሎት ክፍያ ስርዓቱ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የደን ልማቶች የግብርና ምርታማነትን በማጎልበት አረንጓዴ ልማቶችን የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የተፈጥሮ ሀብቶችን ጥበቃና እንክብካቤን በማጠናከር አካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና የህብረተሰቡን ተጋላጭነት መቀነስ አስፈላጊ ነው።
ረቂቅ አዋጁ ለመጀመሪያ ጊዜ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች አካባቢያቸውን በመጠበቃቸው ለአገልግሎታቸው ክፍያ እንዲያገኙ የሚያደርግ የማበረታቻ ስርዓት የሚዘረጋ ነው ብለዋል።
ስነ ምህዳር ላይ ጉዳት የሚያደርሱ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል የአካባቢን ጥበቃ በዘላቂነት የሚያበረታታ ሂደትን የሚፈጥር አዋጅ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙ ባለ ድርሻ አካላት የስነ ምህዳር አገልግሎት አቅራቢዎች፣ ረቂቅ አዋጁ ላይ መካተት የሚገባቸውን ጉዳዮች፣ ግልጽነትን የሚጠይቁና ከትርጉም ጋር በተያያዘ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤በረቂቅ አዋጁ የስነ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ላይ የማህበረሰቡና የባለ ድርሻ አካላት ተጠቃሚነት፣ ተሳታፊነትና ፍትሃዊነት በግልጽ መቀመጡን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ የመንግስት ተቋማትና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት አገልግሎት አቅራቢዎች ይሆናሉ ብለዋል።
ከግብርናና ከደን ልማት ጋር ተያይዞ የስነ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ አስገዳጅ የሆነባቸው አዋጆች መኖራቸውን ጠቅሰው ረቂቅ አዋጁ የክፍያ ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የፌደራልና የክልል ባለ ድርሻ አካላትን ሚና እና ሀላፊነትም በግልጽ አስቀምጧል ብለዋል።
በምክር ቤቱ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር)፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ አሻሚ ትርጉም የሚሰጡ፣ ግልጽነት የጎደላቸው ጉዳዮች ተሻሽለው ጠንካራ አዋጅ እንዲወጣ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።