በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጋ ወራት ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአትክልት እየለማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጋ ወራት ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአትክልት እየለማ ነው
ጊምቢ፤ ህዳር 26 /2018(ኢዜአ) ፡-በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጋው ወራት በመስኖ በመታገዝ ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአትክልት እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ግርማ ጃለታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከመኽር ሰብል ልማት በተጓዳኝ ለበጋ መስኖ ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም በዘንድሮ በበጋው መስኖ 20 ሺህ 532 ሄክታር መሬት በአትክልት መልማቱን ተናግረዋል፡፡
የመስኖ ልማቱ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም አርሶ አደሩ በአመት ሁለቴና ከዚያ በላይ እንዲያመርት ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በበጋ መስኖው በዋናነት ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ቆስጣ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ካሮትና ሌሎች አትክልቶች እየለሙ መሆኑን ጠቁመው ከዚህም 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡
በልማቱም ከ134 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የበጋ የመስኖ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ጠቁመዋል።
የበጋ መስኖ ልማቱ የዞኑን አርሶ አደር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱንና የአመጋገብ ስርአቱን እንዲያሻሽል ማገዙን አንስተዋል፡፡
በመኽር እርሻ ያለሙትን በቆሎ ስብስበው በበጋ መስኖ ጎመንና ቀይስር እያለሙ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጊምቢ ወረዳ ጆግር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጋሩማ ጃለታ ናቸው ፡፡
ከዚህ ቀደም ዝናብን ጠብቀው በማምረታቸው ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር አስታውሰው፤ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን መስኖን በመጠቀም በአመት ሁለቴና ከዚያ በላይ በማምረት የምግብ ዋስትናቸውን እንዳረጋገጡ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የላሎ አሳቢ ሆርዳ ዳሌቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እስራኤል ሁንዱማ በበኩላቸው፤ በግብርና ጽህፈት ቤት በተመቻቸላቸዉ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ አቅርቦት በአካባቢያቸው ካለው ወንዝ ውሀ በመሳብ በጥቂት ጊዜ የሚደርሱ የተለያዩ አትክልቶች እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት በበጋ መስኖ አትክልቶች በማልማት ከቤት ፍጆታቸው አልፈው ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህ አመትም ስራውን ለማስፋት የግብርና ባለሙያዎችን ምክር በመተግበር በበጋ መስኖ ልማት ካሮትና ጥቅል ጎመን እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡