ቀጥታ፡

የአካባቢውን ፀጋ በማልማት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንተጋለን- አመራሮች  

ገንዳውኃ፤ ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ):-  ቅንጅታዊ አሰራርን ይበልጥ አጠናክረው  የአካባቢውን ፀጋ  በማልማት የሕዝቡን ተጠቃሚነት   ለማረጋገጥ  በትጋት እንደሚሰሩ የምዕራብ ጎንደር ዞን አመራሮች  ገለጹ። 

በዞኑ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የተሳተፉበት ሥልጠና "በመደመር መንግሥት እይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ በገንዳውኃ ከተማ እየተሰጠ ነው። 

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በብልፅግና ፓርቲ የምዕራብ ጎንደር ዞን  ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እንዳለው ማሩ እንደተናገሩት፤ ሥልጠናው በየደረጃው ያለውን አመራር ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጎልበት  ያግዛል። 

አመራሩ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለማቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በመገንዘብ ለሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና ስኬት የድርሻውን እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል። 

በመሆኑም እንደ አመራር  አንድ ሆነን የዞኑን ሀብት በማልማት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንሰራለን  ብለዋል። 


 

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ  አቶ እያሱ ይላቅ በበኩላቸው፤ ሥልጠናው  የአመራሩን እውቀት፣ ክህሎት እና አቅም የሚገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

የተግባርና የአስተሳሰብ አንድነትን በመላበስና በሁሉም መስክ በቂ እውቀት በመያዝ ሰላምን አፅንተው  የዞኑን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ አመራር ዘማች ንጉሴ ፤  ሥልጠናውን  በትኩረት ተከታተለው  ተግባር ላይ በማዋል  የወረዳውን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ  ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ከምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የመጡት አመራር ስጦታው አዱኛ በበኩላቸው፤  ሥልጠናው የአመራርነት ሚናን የሚያጎለብት፤ ያላቸውን እውቀትና ክህሎት የሚያዳብር ከመሆኑ ባሻገር አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን አንስተዋል። 

በየደረጃው የሚገኙት አመራሮቹ ቅንጅታዊ አሰራርን ይበልጥ አጠናክረው  የየአካባቢውን ፀጋ  በማልማት የሕዝቡን ተጠቃሚነት   ለማረጋገጥ  በትጋት እንደሚሰሩ  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም