ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል የሰላም ስምምነቱ ልምድና ተሞክሮ የሚወሰድበት ትልቅ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል የሰላም ስምምነቱ ልምድና ተሞክሮ የሚወሰድበት ትልቅ ማሳያ ነው
ወልዲያ/ደብረ ብርሃን፤ ሕዳር 26/2018(ኢዜአ)፡ - በአማራ ክልላዊ መንግስት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ልምድና ተሞክሮ የሚወሰድበት ትልቅ ማሳያ መሆኑን በአማራ ክልል ኢዜአ ያነጋገራቸው የወልዲያ እና የደብረ ብርሃን ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።
የወልዲያ ከተማ ነዋሪው አያሌው ከበደ እንዳሉት፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተደረሰው ስምምነት የሚበረታታና የሚደነቅ ነው።
በስምምነቱ መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ ሕብረተሰቡ ያለ ምንም የጸጥታ ስጋት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መስራትና መኖር እንዲችል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
መንግስት በሆደ ሰፊነት ላበረከተው ላቅ ያለ አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
የሰላም ስምምነቱ በተለይ እንደ ወልዲያ ከተማ ሕዝብ ትልቅ እፎይታን የሰጠ፤ የሰላም አየር የምንተነፍስበትና ስንናፍቀው የነበረ ትልቅ እርምጃ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ የሃገር ሽማግሌ ሲሳይ ጸጋዬ ናቸው።
ስምምነቱ የእናቶችንና የህጻናትን እንግልት ከማስቀረት ባለፈ ለሀገር ግንባታ ድርሻው ከፍ ያለ ነው ያሉት ነዋሪው፤ ይህንን መልካም ተሞክሮ በመውሰድም የቀሩትም ወደ ሰላም አማራጭ ሊመጡ እንደሚገባ አንስተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች መካከል ዋለልኝ አምባው እንዳመለከቱት፤ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ስምምነቱ የሚበረታታ ነው።
ስምምነቱ በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት በማፅናት የሕዝብን የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ ማጎልበት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በተጨማሪም ክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ ፀጋዎች አልምቶ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ተግባራትን ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የተናገሩት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ማቲያስ ክፍሌ ናቸው።
አቶ አማን መሐመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ የነበረው ችግር ሕዝቡን የጎዳ መሆኑን አብስተው፤ ትናንት የተደረሰው ስምምነት ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት መደላድል የፈጠረ ታሪካዊና የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ልምድና ተሞክሮ የሚወሰድበት ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት።
በአማራ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት በትናንትናው ዕለት መፈረሙ የሚታወስ ነው።