ቀጥታ፡

በክልሉ ሀሳብን ከተግባር ጋር በማቀናጀትና የልማት አቅሞችን ወደ ውጤት በመቀየር ለህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይሰራል

ሀዋሳ፤ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ):-ሀሳብን ከተግባር ጋር በማቀናጀት የልማት አቅሞችን ወደ ውጤት በመቀየር ለህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትጋትና በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የሲዳማ ክልል አመራሮች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ማጠቃለያ ላይ በሰጡት የስራ አቅጣጫ፥ አመራሩ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በመፍጠን፣ በመፍጠር፣ በማባዛትና በማጥራት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ስልጠናውን የተከታተሉ የሲዳማ ክልል አመራሮችም ሀሳብን ከተግባር ጋር በማቀናጀት የልማት አቅሞችን ወደ ውጤት በመቀየር ለህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትጋትና በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ሰለሞን እንደተናገሩት፥ ስልጠናው የወቅቱን ፈተናና የልማት ፍላጎቶችን በተገቢው ተረድቶ መፍትሄውን በኃላፊነትና በላቀ ቁርጠኝነት ለመፈለግ ተደማሪ አቅም ፈጥሯል፡፡

በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ስራ ላይ በማዋል በክልሉ የከተሞችን አቅም ወደ ተግባር በመቀየር ለነዋሪውና ለስራ እድል ፈጠራ የተመቹ እንዲሆኑ እያደረጉ ያለውን ጥረት በማጠናከር ለመስራት ማቀዳቸውን አስረድተዋል።

በክልሉ ወደ ከተሜነት የተጠቃለሉ ከ73 በላይ ከተሞች ከገጠሩ ክፍል ጋር ተሳስረውና ተሰናስለው ማደግ እንዲችሉ የሚያስችል ግብ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ከተማና መሰረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ምንትዋብ ገብረመስቀል በበኩላቸው፥ ስልጠናው የክልሉን የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ በማልማት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የልማት ዕድሎችን ወደ ውጤት ለመቀየር አመራሩ በትጋት የሚሰራበትን አቅም ያጠናከረ መሆኑን ጠቅሰው፥ለዚህም የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን በማጠናከር የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ደምሴ ዶንጊሶ በበኩላቸው፥በከተማው በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝምና ግብርና እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ አቅሞችና ዕድሎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በመፍጠን፣በመፍጠር፣ በማብዛትና በማጥራት መርህ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት እንደሚሰሩም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም