የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ በየትኛውም መልኩ የኃይል አማራጭ ተቀባይነት እንደሌለው ትምህርት የሚሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ በየትኛውም መልኩ የኃይል አማራጭ ተቀባይነት እንደሌለው ትምህርት የሚሰጥ ነው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ)፡-የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውጪ ያለው የኃይል አማራጭ ተቀባይነት እንደሌለው ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተስፋሁን አለምነህ ገለጹ።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል ዘላቂ የሰላም ስምምነት ትናንት ተፈርሟል።
የሰላም ስምምነት ሂደቱን ሲያስተባብሩና ሲያደራድሩ የቆዩት የአፍሪካ ሕብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ናቸው።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዲኃን) ሊቀ መንበር እና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተስፋሁን አለምነህ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሰላም ዋጋ በምንም የማይተካ ነው።
በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ ማንኛውም ስምምነቶች በሁሉም ወገን የሚደገፉና ሌሎች አካላት በተመሳሰይ ሊከተሉት የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል።
የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አንስተዋል።
የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ ለህዝቡ እፎይታ የሚሰጥ ከመሆኑ አኳያ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንዲመለሱ ያደርጋል ብለዋል።
የፖለቲካ ጥያቄያቸውን በትጥቅ ትግል ለማስመለስ የሚፈልጉ ሃይሎችም ከዚህ በመማር ወደ ሰላም እንዲመጡ ጠይቀዋል።
የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውጪ ያለው አማራጭ ተቀባይነት እንደማይኖረው ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱ በአፍሪካ ህብረትና በኢጋድ ጥላ ስር መካሄዱም አህጉራዊ አቅሞችን በመጠቀም ችግሮችን የመፍታት አቅምን ማሳያ ነው ብለዋል።
ችግሮችን በውይይትና በድርድር መፍታት የሰለጠነ ፖለቲካ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፥በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የትጥቅ ትግልን የመረጡ ሃይሎች ይህን ወርቃማ ዕድል እንዲጠቀሙና የበደሉትን ህዝብ እንዲክሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የፌዴራል መንግሥትና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።