ቀጥታ፡

አዲሱ ቴክኖሎጂ ተቋሙን ወደ ተሟላ የዲጂታል አገልግሎት ስርዓት ያሸጋግራል

አዲስ አበባ ፤ ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ)፡-አዲሱ የተቀናጀ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ቴክኖሎጂ ተቋሙን ወደ ተሟላ የዲጂታል አገልግሎት ስርዓት የሚያሸጋግር መሆኑን  ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የለማውን የተቀናጀ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ዲጂታል ስርዓት ዛሬ አስጀምረዋል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ስር ነቀል ለውጥ ከተመዘገበባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ነው፡፡

በተለያዩ ዘርፎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋቱ ነዋሪዎችን ከአላስፈላጊ የገንዘብ እና የጊዜ ብክነት ለመታደግ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

አገልግሎቱ ይፋ ያደረገው በዲጂታል የታገዘ የአሰራር ስርዓት የተቀናጀ እና የዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው አስታወቀዋል፡፡

እንዲሁም ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል፡፡


 

አዲስ የለማው የዲጂታል ስርዓት የፋይዳ እና የነዋሪነት መታወቂያን በአንድ ላይ አቀናጅቶ የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ማንኛውም ግለሰብ በስማርት ስልክ በመታገዝ ከጎግል ፕላይ ስቶር እና ከአፕል ስቶር በማውረድ መጠቀም እንደሚችል ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው ከተቋሙ የሚመነጩ መረጃዎችን በመሰነድ ትክክለኛ ፖሊሲ ለመቅረጽ እና እቅድ ለማዘጋጀት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

ዲጂታል ስርዓቱ የአዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድገው ጠቅሰው ከሕዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በ50 ወረዳዎች ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ብለዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የእድገት ማቀጣጠያ መሳሪያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ አያሌ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ በዚህም በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡


 

አዲሱ ቴክኖሎጂ የተቋሙን የአገልግሎት ጥራት የሚያሳድግ እንዲሁም ብልሹ የአሰራር ስርዓትን የሚያስወግድ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሴ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም