በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ቀኑ በስኬት እንዲከበር የድርሻቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ቀኑ በስኬት እንዲከበር የድርሻቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል
ሆሳዕና ፤ ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ የሚከበረው 20ኛው የብሔሮች ብሔረሰብችና ህዝቦች ቀን በዓል ስኬታማ እንዲሆን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን የምታስተናግደው ሆሳዕና ከተማ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንግዶቿን ለመቀበል ተዘጋጅታለች።
በዓሉን በማስመልከት ኢዜአ በከተማው ያነጋገራቸው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና የከተማው ነዋሪዎችም በዓሉ በስኬትና በድምቀት እንዲከበር የሚያስችል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከወጣቶቹ መካከል ሎብዱኖ በየነ እንደገለጸው፤ እንደሀገር በከተማው የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ደማቅና ስኬታማ እንዲሆን የበኩሉን ለመወጣት ተዘጋጅቷል።
በዓሉ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት እሴት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ በሰላማዊና በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ከሌሎች ወጣቶችና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግሯል፡፡
የማህበረሰቡ አብሮነትና ሕብረብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር በማድረግ በኩል የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጾ፣ ለበዓሉ ወደከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተቀብሎ ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ሌላኛዋ በጎ ፍቃደኛ ወጣት መስከረም አድማሱ በበኩሏ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ኢትዮጵያውያን በጋራ ደምቀን የምንታይበት ነው ብላለች፡፡
በዓሉ የኢትዮጵያዊያንን የተለያዩ ቱባ ባህሎች በአንድ ቦታ ለማየትና እሴቶቻቸውን አጉልተው እንዲያወጡ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም ገልጻለች።
ለበዓሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ከመቀበል ጀምሮ በከተማዋ በሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ በማድረግ በዓሉን በአብሮነት እንዲያከብሩ የበኩሏን እንደምትወጣ ገልጻለች።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ለዘመናት የቆየውን የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነትና ትስስር እንዲጠናከር የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በከተማው የሄጦ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ልዩወርቅ ከበደ ናቸው።
እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድ ኢትዮጵያዊያን ከምንታወቅባቸው መገለጫዎች አንዱ ነው በማለት ወደ ሆሳዕና የሚመጡ እንግዶችን እንደ ቤተሰብ ከማስተናገድ ባለፈ በዓሉ ደማቅና ሰኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ካሳ በበኩላቸው፤ ለ20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንግዶች ወደሆሳዕና ከተማ እንደሚመጡ ገልጸዋል።
እንግዶቹ በከተማዋ በሚኖራቸው ቆይታ በዓሉን በነጻነት ተንቀሳቅሰው ማክበር እንዲችሉ የተለያዩ አካላትን ያሳተፈ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ለበዓሉ ስኬታማነት ከጸጥታ አካል በተጨማሪ ከ400 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና ወስደው የሥራ ስምሪት እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡
ወጣቶቹ ለእንግዶች አቀባበል ከማድረግ ባለፈ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ አቅጣጫ በመጠቆምና በተለያየ መንገድ ድጋፍ በማድረግ ለበዓሉ ስኬት የድርሻቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል።