ቀጥታ፡

በክልሉ ሙስናን የመከላከልና የሥነ ምግባር ግንባታ ሥራዎች ይጠናከራሉ

ሚዛን አማን፤ ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል አገልግሎትን የማዘመንና የሥነ ምግባር ግንባታ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የክልሉ ሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አመለከተ።

"ትውልድን በሥነ ምግባር ተቋምን በአሠራር" በሚል መሪ ሐሳብ 21ኛው የጸረ ሙስና ቀን በክልል ደረጃ በሚዛን አማን ከተማ ተከብሯል። 

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ በወቅቱ እንዳሉት፤ ሙስና ልማትን የሚያስተጓጉልና ተቋምን የሚያዳክም እኩይ ተግባር በመሆኑ ለሀገር ዕድገት እንቅፋት ነው።


 

በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የተጀመረውን ስራ ቀጣይነት ለማረጋገጥ አገልግሎትን ለማዘመንና ለሥነ-ምግባር ግንባታ ሥራዎች ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የሙስና መከላከል ተግባር እያከናወነ ሲሆን በ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ከምዝበራ ማዳን መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ሙስናና ብልሹ አሠራርን በዘላቂነት ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር የሕዝብ ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ 

በዚህም በትምህርት ቤቶችና ሌሎች የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች ስለሙስና አስከፊነትና የመከላከል ሥራ ግንዛቤ የመፍጠርና ተያያዥ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ግብረ ኃይል በማቋቋም በተሰራ ሙስናን የመከላከል ተግባር የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ከማሳደግ ባሻገር የህዝብና የመንግሥት ሀብትን ከብክነት በመታደግ ረገድ ውጤታማ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሤ ወ/ጊዮርጊስ ናቸው። 


 

ይህን ተግባር ለማጠናከር የሀገር መሠረት የሆኑ ወጣቶችን በሥነ ምግባር መገንባት እና የሀሳብ እና ተግባር አንድነት ይዞ ብልሹ ተግባርን ማስወገድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከቤተሰብ ጀምሮ በትውልድ ቀረጻና ሙስናን በድፍረት በማጋለጥ ተግባር ላይ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም አሳስበዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ወልደ ገብርኤል ሽፈራውና ኢንስፔክተር አድነው አሰፋ በሰጡት አስተያየት፤ ሙስናን የመከላከል ተግባር ውጤታማ እንዲሆን የመንግሥትና ሕዝብ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል።


 

ብልሹ አሠራርን ዳር ቆሞ የመመልከትና ታዝቦ ብቻ የማለፍ ባህል ሀገር ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል ሊያበቃ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡


 

ወይዘሮ አልማዝ ደምሴ የተባሉ ሌላኛዋ የበዓሉ ታዳሚ በበኩላቸው፤ከሙስና የጸዳች ሀገር ለመፍጠር ሁላችንም ከቤት ጀምረን ልጆቻችንን በሥነ ምግባር አንጸን ማሳደግ አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም