ቀጥታ፡

አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከምና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት ይጠናከራሉ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2018(ኢዜአ)፦ አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከምና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት የመጠቀም ባህልን በማሳደግ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በግብርና ሚኒስቴር የአፈር ሀብት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ሊሬ አቢዮ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የአፈር ለምነትን መጠበቅና መንከባከብ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአሲዳማ የተጠቃ መሬት በሰብል ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰዋል።


 

በተለይም በኦሮሚያ፣ አማራ፣ በሲዳማ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በአሲዳማ አፈር የተጠቃ ሰፊ መሬት መኖሩን ተናግረዋል።

እንደ ሀገር አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከምና የአርሶ አደሮችን የተፈጥሮ ማዳበሪያ የመጠቀም ባህል በማሳደግ የሰብል ምርታማነትን የሚያሻሽል የአፈር ለምነት ጥበቃና የመንከባከብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ የሚሰሩ ስራዎች በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመዘገብ አቅም እየፈጠሩ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች እቀባ የእርሻ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በአፈር ለምነትና ጤንነት ጥበቃ ላይ በሰፊው እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በዚህ ቴክኖሎጂም አርሶ አደሩ የተሻለ ምርት እንዲያገኝ ማስቻሉን ገልጸዋል።


 

በእቀባ እርሻ ቴክኖሎጂ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ አካባቢ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በክልሎቹ የተመዘገበውን ተጨባጭ ለውጥ ወደ ሌሎች ክልሎች ለማስፋት ለአርሶ አደሮችና ለዘርፉ ተዋናዮች ተሞክሮዎችን የማጋራትና የልምድ ልውውጥ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የአፈር አሲዳማነት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በተሰራው ስራ ምርታማነትን ማሻሻል የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ገልፀዋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርና የተቀናጀ የአፈርና የውሀ ጥበቃ ስራ ለአፈር ለምነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ መሪ ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም