የሰላም ስምምነቱ ግጭትን በዘላቂነት የሚፈታ በመሆኑ እፎይታና ደስታ ሰጥቶናል - የባሕርዳር ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱ ግጭትን በዘላቂነት የሚፈታ በመሆኑ እፎይታና ደስታ ሰጥቶናል - የባሕርዳር ነዋሪዎች
ባሕርዳር፤ ሕደር 26/2018(ኢዜአ)፡- የሰላም ስምምነቱ በክልሉ የነበረውን ግጭት በዘላቂነት የሚፈታ በመሆኑ እፎይታና ደስታ ሰጥቶናል ሲሉ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል ትናንት ዘላቂ የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል።
በዚህ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች፣በነበረው ግጭት አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞን ቆይተናል ብለዋል።
በየመድረኮችና በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር ችግሩ በሰላም እንዲቋጭ በተደጋጋሚ ጥያቄ ስለመቅረቡ አውስተው፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስንጠይቅና ስንመኘው የነበረው ሰላም የመፍጠር ጉዳይ ምላሽ በማግኘቱ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ሲሉ ገልጸዋል።
በክልሉ መንግስትና አፋሕድ መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት በመፈረሙ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል፡፡
የችግሮች ሁሉ መቋጫው በውይይትና መግባባት ሰላም መፍጠር መሆኑን አንስተው ፤ ለሰላም ቁርጠኛ አቋም ይዘው ለሰሩትና የተግባር ሰዎች ሆነው ለተገኙት ሁሉ ምስጋና እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
ከባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሼሕ መሀመድ ኢብራሂም እንዳሉት፤ ትናንት የክልሉ መንግስት እና የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል የተደረሰው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ችግርን ተቀራርቦ በመግባባት መፍታት እንደሚቻል አስተማሪና አርአያነት ያለው ማሳያ እንደሆኑ ተናግረዋል።
የከተማዋ ነዋሪ አቶ ደሳለኝ እሸቴ በበኩላቸው ፤ የሰላም ማጣት ችግር በክልሉ ሕዝቡ ከቦታ ቦታ እንደልብ ተንቀሳቅሶ እንዳይሰራ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ችግርን በውይይትና በንግግር ለመፍታት በተደረሰው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ይህም ለክልሉ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና እድገት መፋጠን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ የቀሩትም በቀረበላቸው የሰላም አማራጭ እድል እንዲጠቀሙ ይበልጥ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምነቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ያመቻቸ በመሆኑ እንደሚደግፉት የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ አወቀ ዕምሬ ናቸው።
ችግሩ በሰላም እንዲቋጭ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደቆዩ ያወሱት ነዋሪዎቹ፤ ይህም እውን ሆኖ ምላሽ በማግኘቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የሰላም ስምምነቱ ግጭትን በዘላቂነት የሚፈታ በመሆኑ እፎይታ ሰጥቶናል ያሉት ነዋሪዎቹ ለሰላም ቁርጠኛ አቋም ይዘው ለሰሩትና የተግባር ሰዎች ሆነው የተገኙት ሁሉ ሊመሰገኑ እንደሚገባም ተናግረዋል።