በሲዳማ ክልል ያለውን የማዕድን ሀብት በመለየት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ያለውን የማዕድን ሀብት በመለየት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሀዋሳ ፤ ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ያለውን የማዕድን ሀብት በመለየት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ገለፀ ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመደመር መንግስት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው የአመራሮች ሥልጠና ላይ በሰጡት ማብራሪያ የማዕድን ዘርፍ እንደ ሀገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡
በማብራሪያቸው ዘርፉ በዕቅድና በዕውቀት መመራት እንዳለበት እንዲሁም የፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱ አቅምን ያገናዘበ ሊሆን እንደሚገባው ማሳሰባቸውም እንዲሁ፡፡
የማዕድን ሀብት ልማት ለኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን መሰረት ከመሆኑም ባሻገር ጅማሮው ተስፋ ሰጪና በቀጣይ የማዕድን ዘርፉ የኢትዮጵያ በረከት እንደሚሆንና ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ሊሆን እንደሚችል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ መረዳት ይቻላል።
ይህንንም ከግምት ያስገባው የሲዳማ ክልል የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ በክልሉ ያለውን የማዕድን ሀብት በመለየት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።
በቢሮው የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን መጩካ እንደገለፁት፤ የማእድን ሃብትን በማልማት ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለሀገር እድገት መሰረት እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ቢሮው ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና ከጂኦሎጂካል ኢንስትቲዩት ጋር በመተባበር መጠነ ሰፊ ጥናት በማከናወን ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በጥናቱም ባለፉት ሶስት ዓመት ብቻ ግራናይት፣ ማርብል፣ አይረን፣ ከሮሜት እና ሊቲየምን ጨምሮ 17 የሚሆኑ ማዕድናት በልየታ መገኘታቸውን አብራርተዋል ፡፡
በአሁኑ ወቅት ወርቅ የማውጣት ሥራው እየተከናወነ ያለው በሆኮ እና ጫቤ በተባሉ ወረዳዎች ላይ መሆኑን ጠቅሰው ወርቅ የማውጣቱ ሥራ በኢንተርፕራይዝ በተደራጁ ወጣቶች አማካይነት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
ከዚህ ቀደም ከክልሉ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን ከ15 ኪሎ ግራም የማይበልጥ የነበረውን ሂደት ለመቀየር ሕገ-ወጥነትን በመከላከል ላይ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በጥናት የተለዩ ግራናይት፣ ማርብልና መሰል ማዕድናትን ለማውጣት በርካታ ባለሀብቶች ፈቃድ ማግኘታቸውንና ምርት ለማምረት በተለያዩ የዝግጅት ደረጃዎች ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ከክልሉ 192 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበ ሲሆን ዘንድሮ እስከ ህዳር ወር አጋማሽ ብቻ ከ532 ኪሎ ግራም ወርቅ መቅረቡም ተመልክቷል።