ቀጥታ፡

ስምምነቱ ሰላም እንዲፀና ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው 

ደብረማርቆስ / ደሴ  ፤ ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ)፦   የተደረሰው የሰላም ስምምነት  ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታ  የፈጠረ ነው ሲሉ የደብረ ማርቆስ እና ደሴ ከተሞች  የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አስታወቁ። 

በአማራ ክልላዊ መንግስትና  በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት(አፋሕድ ) መካከል  የዘላቂ ስምምነት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ኢዜአ በደብረ ማርቆስ እና ደሴ ከተሞች ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ፤በስምምነቱ  ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውና ለሕዝቡም እረፍት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ ርዕሰ ርዕሳን አባ ሃይለማሪያም ታገለ ፤ የሰላም ስምምነት ቀን እንዲመጣ አበክረን ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል።


 

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን አንስተው፤ ችግሮችን በሰለጠነ  መንገድ በመነጋገር መፍታት ስልጡንነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት  መካከል የተደረሰው  ስምምነት ሰላምን በዘላቂነት አፅንቶ  ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

የእምነት አባቶች ፍላጎት እና ጥረትም ይህ መሆኑን አንስተው፤ የቀሩትም ይህን የተቀደሰ ተግባር  እንዲከተሉ መክረዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪው ሸህ ሙሃመድ ሙሳ በበኩላቸው፤ ስምምነት መደረጉ እኛ የሃይማኖት አባቶች በጉጉት ስንጠብቀው እና ስንሰብከው የነበረው ተግባር በመሳካቱ ተደስተናል ብለዋል።


 

የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አድንቀው፤  በዚህም መንግስት ምስጋና ሊቸረው የሚገባ መሆኑን  ገልጸዋል።

ስምምነቱ ለክልሉ ብሎም እንደ ሃገር ልማትን ለማፋጠን ይበልጥ የሚያነሳሳ እና አስተማሪ የሆነ ተግባር እንደሆነም አንስተዋል።

ጫካ የቀሩትም ይህንን የሰላም መንገድ እንዲከተሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቤተክርስቲያን ሰላም እንዲሰፍን ትፈልጋለች የሃይማኖት አባቶችም ሰላምን አጥብቀን በመስበካችን የሰላም ስምምነቱ በመሳካቱ አስደስቶኛል ያሉት ደግሞ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ላቀው ናቸው።

በተመሳሳይ የደሴ ከተማ ነዋሪ  ሸህ መሀመድ ሙሳ በበኩላቸው፤ የሰላም ስምምነቱ ሕብረተሰቡን ከስጋት የታደገ፣ መለመድና መቀጠል ያለበት ተግባር ነው ብለዋል።


 

በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሕብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ ልጆቻችን ያለ ስጋት እንዲማሩ፣ ነጋዴው ተረጋግቶ እንዲነግድ፣ አርሶ አደሩ ሳይቸገር ማምረት እንዲችል ሲመክሩና ሲወያዩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ውይይታችንና አባታዊ ምክራችን ፍሬ እያፈራ  ከመሆኑ ባለፈ የትላንቱ ስምምነትም  ስንመኘው  የቆየነው  ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታ  የፈጠረ  መሆኑን ገልጸዋል።

የትኛውም ግጭት መቋጫ ውይይትና ንግግር መሆኑን አስታውሰው ፤ ሁሉም ለሰላምና ለንግግር ቅድሚያ በመስጠት ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል  በጋራ መትጋት እንዳለበት አመልክተዋል። 


 

ሌላው የሀገር ሽማግሌ አቶ ልዑል ይማም፤  ስምምነቱ ሰላምን ለማጽናት እያደረግን ያለው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ማሳያ ነው ብለዋል።

አሁንም ቀሪ በጫካ ያሉት ወደ ሰላም እንዲመጡ ያልተቋረጠ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቁመው፤ ስምምነቱ ለሕዝቡ እፎይታን የሰጠ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም