ቀጥታ፡

የተቀናጀ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ዲጂታል ስርዓት ነዋሪዎች ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2018 (ኢዜአ)፡- የተቀናጀ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ዲጂታል ስርዓት ነዋሪዎች ዘመናዊ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቱዩት የለማውን የተቀናጀ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ዲጂታል ስርዓትን ዛሬ አስጀምረዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዲጂታል ስርዓቱ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ተገልጋዮች ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ ነው።

ከዚህ በፊት የነበረውን የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎችን አገልግሎት አሰጣጥ ሙሉ በሙሉ የሚቀይር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዲጂታል ስርዓቱ የአዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ መሆኑን በማንሳት፤ ከሕዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በ50 ወረዳዎች ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቱዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፤ እንደ ሀገር ፈጣን ዕድገት ለማስመዝገብ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍና ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸው፤ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች ነው ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም