ቀጥታ፡

ስምምነቱ ዘላቂ ሰላም ከመፍጠር ባለፈ ለወጣቱ እፎይታን የሰጠ ነው

ደሴ/ወልዲያ፤ ሕዳር 26/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል የተደረሰው ስምምነት ዘላቂ ሰላም ከመፍጠር ባለፈ ለወጣቱ እፎይታ የሰጠ ነው ሲሉ የደሴና ወልዲያ ከተሞች ነዋሪ ወጣቶች ተናገሩ።

በስምምነቱ ዙሪያ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በደሴ ከተማ ያነጋገራቸው ወጣቶች እንደገለጹት፣ ስምምነቱ ሲመኙት የነበረ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው።

ከደሴ ከተማ ወጣቶች መካከል አንዋር ካሳው ስምምነቱ ስንመኘው የነበረ በመሆኑ ተደስተናል ብሏል።

ግጭት ጥፋትና ውድመት እንጂ መፍትሄ እንደማያመጣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተግባር አይተነዋል ሲል ወጣቱ አንስቷል።

የተደረሰው የሰላም ስምምነቱ ዘርፈ ብዙ ችግር ከማቃለል ባለፈ የተሟላ ሰላም እንዲሰፍን በማስቻል በተለይ ለወጣቱ እፎይታን የሰጠ መሆኑን ተናግሯል።

ሌላው ወጣት ሰዓዳም አሊ፤ ስምምነቱ ሕዝቡን ከጉዳት በመታደግ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎችም ተቋማት ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን ግልጋሎት ማጠናከር የሚያስችል ብሎ ልማት እንዲቀጥል የሚያደርግ በመሆኑ ተደስተናል ብሏል።

በጫካ የቀሩ ወገኖች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ሰላምን ሊያጠናክሩ ይገባል ያለው ወጣቱ፣ ጥያቄ ቢኖራቸው እንኳ በንግግር መፍታት ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

የተፈጠረው የሰላም ስምምነት ተረጋግተን እንድንሰራ፣ በሰላም ወጥተን እንድንገባ፣ እንድንማር፣ እንድንታከም፣ ልማት እንዲፋጠን ከማድረጉ ባለፈ ወጣቱ የግጭት ሰለባ እንዳይሆን የሚያስችል ነው ያለው ደግሞ ወጣት ሰይድ ሞላ ነው።

ስምምነቱ ታሪካዊ ጠላቶችን በማሳፈር ወዳጆቻችንን ደግሞ ያስደተና እፎይታ የሰጠ ነው፤ የውስጥ ችግሮቻችንን በራሳችን መፍታት እንድምንችል ማሳያ ነው ብሏል።

በተመሳሳይ ከወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ ወጣት ኤፍሬም አያሌው፤ የሰላም ስምምነቱ ለወጣቱ ሰላማዊ ህይወት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው ሲል ገልጿል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበሩ ግጭቶች ዋነኛ የጥቃት ሰለባ ወጣቱ እንደነበር ጠቅሶ፤ የተደረሰው የሰላም ስምምነት የሚያስደስትና እፎይታ የሰጣቸው መሆኑን ገልጿል።

ሌላው የወልዲያ ከተማ ወጣት ጥላሁን ኃይሌ፤ የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን የሚያስቀር ትልቅ የምስራች ነው ብሏል።

እንደፈለግሁ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሬ ቤተሰቤን ለመምራት የሚያስችል ስምምነት በመሆኑ ልዩና ታሪካዊ ቀን አድርጌ ወስጀዋለሁ ያለው ወጣቱ፤ ሰላም በዘላቂነት ፀንቶ እንዲቀጠል የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

በክልሉ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል ትናንት የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም