ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት ዕይታን በተግባር በማዋል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመሪነት ሚናችንን እንወጣለን- አመራሮች

አሶሳ፤ ህዳር 26/2018(ኢዜአ)፦  የመደመር መንግሥት ዕይታን  በተግባር  በማዋል  የህብረተሰቡን  ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  የመሪነት ሚናቸውን እንደሚወጡ   የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች ተናገሩ።

ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች "በመደመር መንግሥት ዕይታ! ለዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ ስልጠና ተሰጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለከፍተኛ አመራሮች በተሰጠው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ በሰጡት ገለጻ የመደመር መንግሥት የሚፈጽማቸውን የልማት ግቦች በዝርዝር በማስረዳት በየደረጃው ያለው አመራርና አጠቃላይ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ታክሎበት ለተግባራዊነቱ እንዲተጉ አስገንዝበዋል።

በየአካባቢው የሚገኙ ሀብቶችን በማልማት የህዝብን ተጠቃሚነትና የብልጽግና ጉዞን ለማረጋገጥ የአመራሩ ሚና ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ማስገንዘባቸው ይታወሳል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስልጠናውን የወሰዱ አመራሮችም ያገኙትን ስልጠና ተግባራዊ በማድረግ የመሪነት ሚናቸውን በተናበበ ሁኔታ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ከሰልጣኝ አመራሮች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገጠር ቴክኖሎጂ ብዜትና የግብርና ሜካናይዜሽን ማስፋፊያ ኤጄንሲ ዳይሬክተር ሙስጠፋ ሙሐመድ፤ ስልጠናው ሀገራዊ ዕቅዶችን ወደ ተግባር ለመቀየር አቅጣጫ የሚጠቁም እና የአመራሩን ሚና በግልጽ ያመላከተ እንደነበር ገልጸዋል።

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የአመራሩን የተግባርና የአመለካከት ቅንጅት መጠየቁን አንስተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች እና ሰው ተኮር ስራዎች አሁን ለተጀመረው ተሻጋሪ የመደመር ትውልድ እሳቤ ምሳሌ ናቸው ያሉት አቶ ሙስጠፋ በሁሉም ዘርፍ ቀጣይነት ያለው ልማት ለማከናወን የሚያስችል ስልጠና ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

ሌላዋ ሰልጣኝ አመራር የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ ኃላፊ ሀጂራ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ስልጠናው ሀገራዊና ክልላዊ የልማት ዕቅዶች ለማስፈጸምና ለመፈጸም ለአመራሩ ተጨማሪ አቅም የፈጠረ ነው ብለዋል።

አመራሩ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ራሱን ማዘጋጀት እና ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

በከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በላቀ አፈጻጸም እና ተነሳሽነት ለማከናወን የሚያስችል ተጨማሪ አቅም ማግኘታቸውን አክለዋል።

ስልጠናው በይበልጥ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሚደግፉት ግብርና፣ ቱሪዝም እና ኢንዱስትሪ ላይ ያተኮረ መሆኑ ወደ ብልጽግና ለሚደረገው ጉዞ አጋዥ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ አመራር በብልጽግና ፓርቲ ቤኒሻንጉል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የወረዳ ሁለት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጉደታ ነጋሳ ናቸው።

ስልጠናው እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ መሰጠቱ አመራሩ የጋራ አረዳድ እንዲይዝ እና በስራው ስኬታማ እንዲሆን  እንደሚያግዝና  ራሳችንን በመፈተሽ ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የክልሉን ሀብት ወደ ልማት በመቀየር የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽል ተጨባጭ ስራ ለመስራት አመራሩ የመፍጠር እና የመፍጠን እሳቤን ለመተግበር ዝግጁ መሆኑን አቶ ጉደታ ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም