በመደመር መንግሥት ዕይታዎች በጠንካራ ትብብርና አንድነት ለጋራ እድገትና ብልጽግና እንሰራለን - ከፍተኛ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር መንግሥት ዕይታዎች በጠንካራ ትብብርና አንድነት ለጋራ እድገትና ብልጽግና እንሰራለን - ከፍተኛ አመራሮች
ሐረር፤ ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ)፦ በመደመር መንግሥት ዕይታዎች በጠንካራ ትብብርና አንድነት ለጋራ እድገትና ብልጽግና እንሰራለን ሲሉ የሐረሪ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለከፍተኛ አመራሮች ስልጠና እና የስራ አቅጣጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
በማብራሪያቸውም የመደመር መንግሥት የሚፈጽማቸውን የልማት ግቦች በዝርዝር በማስረዳት በየደረጃው ያለው ዓመራርና አጠቃላይ የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ ታክሎበት ለተግባራዊነቱ እንዲተጉ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔና ቀጣይ መዳረሻ ታሳቢ በማድረግም የመደመር መንግሥት የመፍጠን፣ መፍጠር፣ ማባዛትና ማጥራት እሳቤዎችን በመሰነቅ ለተግባራዊነቱ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዚህም የአመራሩ የመፈፀም ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ምን ይመስላል በማለት ኢዜአ በሐረሪ ክልል የተለያዩ አመራሮችን አነጋግሯል።
አመራሮቹም በመደመር መንግሥት ዕይታዎች በጠንካራ ትብብርና አንድነት ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት በላቀ ትጋት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የመደመር መንግሥት የብዝሃ ዘርፍ ዕይታዎች ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ከድህነት የሚያወጡ መሆናቸውን በስልጠናው ተገንዝበናል፤ ለስኬቱም የላቀ ሚናችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የክልሉ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብሳ ኢብራሂም፤ የመደመር መንግስት እምቅ አቅሞችን በማልማት ከድህነት ለመውጣት በጠንካራ ትብብር የሚሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የሀገርን ብዝሃ ጸጋና አቅሞች በማሰባሰብ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በዲጂታል ዘርፎች እመርታዊ ስኬት መመዝገቡንም ገልጸዋል።
አመራሩ በመደመር መንግስት ዕይታዎች በጠንካራ ትብብርና አንድነት ለጋራ እድገትና ብልጽግና እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የክልሉ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብይ አበበ፤ የመደመር መንግስት እይታዎች በተለይም ለአርሶ አደሩ መሰረታዊ ለውጥና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ከግብርና ባለፈ ለኢንዱስትሪው ማንሰራራትና የተሳሰረ ልማት ጽኑ መሰረት የሚያኖርና እድገትና ማንሰራራትን የሚያመጣ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በተለይም በአመራሩ ትጋት፣ በመፍጠርና በመፍጠን መከናወን አለባቸው ተብለው የተያዙ የጋራ ግቦች እንዳሉ ጠቅሰው ለስኬቱ በላቀ ትብብርና አብሮነት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ታመነ ፍቃዱ፤ የመደመር መንግስት መዳረሻው የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ በመሆኑ ይህንን እውን ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የተያዘውን አቅጣጫ በመከተል፣ በመደመርና በተግባር ተኮር ስራዎች ለውጤት እንተጋለን ሲሉ አረጋግጠዋል።