ቀጥታ፡

የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለህዝብ የሰላም ጥያቄ ምላሽ የሰጠና ለዘላቂ ሰላም ሁነኛ መፍትሄ ነው - ወጣቶች

ሰቆጣ ፤ህዳር 26/2018 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል መንግስትና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለህዝብ የሰላም ጥያቄ ምላሽ የሰጠና ለዘላቂ ሰላም ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገለጹ።

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል በትናንትናው እለት የዘላቂ የሰላም ስምምነት የተፈረመ መሆኑ ይታወቃል።

ከስምምነቱ በኋላ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ በግጭት የሚመጣ ውጤት አለመኖሩንና አሸናፊም ተሸናፊም የማይኖር መሆኑን አንስተው ሰላም ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን በመወከል ንግግር ያደረጉት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ መሆን ከባንዳነት በስተቀር ሌላ መገለጫ የለውም ብለዋል።

በመሆኑም የሰላም ስምምነቱ ሁሉንም አሸናፊ ያደረገና በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች እንዳሉት የሰላም ስምምነቱ የህዝብን የጸና የሰላም   ፍላጎት መሰረት ያደረገና ዘላቂ መፍትሄም የሚያመጣ ነው።  

የከተማው ነዋሪ ወጣት ጥላሁን አበበ  እንዳለው በክልሉ ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወጣቱ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብቱ በመገደቡ ለችግር ተዳርጎ የቆይቷል።

 የተደረሰው ስምምነት የህዝቡን የጸና የሰላም ፍላጎት መሰረት ያደረገና በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አቅም የሚፈጥር መሆኑን አመልክቷል።

የወጣቱን ተንቀሳቅሶ የመስራትም ሆነ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም አመልክቷል ።

 የተደረሰው ስምምነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወጣቱ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለው ገልፆ ከሃሰተኛና አፍራሽ አጀንዳዎች እንዲጠበቅ መክሯል።

ወጣት ፋሲካ አማረ በበኩሏ ስምምነቱ  ለህዝብ የሰላም ጥያቄ ምላሽ የሰጠና ለዘላቂ ሰላም መስፈን ሁነኛ መፍትሄ ነው ብላለች።

የህዝብ ፍላጎት ሰላም ነው ያለችው ወጣት ፋሲካ ስምምነቱም ይህንኑ በተግባር ያረጋገጠ ስለመሆኑ  አመልክታለች።

የሰላም ስምምነቱ ህዝቡን ከችግርና ከሰቆቃ የሚታደግ መሆኑን ጠቁማ በተለይም ወጣቱን ከሰቀቀን ያወጣና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጻለች።

 በግጭት እልቂትና ውድመት እንጅ ለውጥ አይመጣም ያለው ደግሞ ሌላው ወጣት ፋሲካ አሰፋ ነው።

ስምምነቱ ግጭትን ከመሰረቱ የሚያስቀርና ሰላምን በዘላቂነት የሚያጸና በመሆኑ መደሰቱን ገልጿል።

በተለይም ወጣቱ ከሰላም ስምምነቱ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆን አስታውቋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም