የሰላም ስምምነቱ የሰላም ችግር እንዲያበቃ ተግባራዊ ምላሽ የተሰጠበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱ የሰላም ችግር እንዲያበቃ ተግባራዊ ምላሽ የተሰጠበት ነው
ገንዳ ውኃ፤ ሕዳር 26/2018(ኢዜአ):- የተደረሰው የሰላም ስምምነት የህዝብ የሰላም ችግር እንዲያበቃ ተግባራዊ ምላሽ የተሰጠበት ነው ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ የሀይማኖት አባቶች ተናገሩ።
በትናንትናው ዕለት በአማራ ክልል መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል።
በዚህ ዙሪያ ኢዜአ በገንዳ ውኃ ከተማ ካነጋገራቸው መካከል የሀይማኖት አባት መልዓከ ኃይል ዘሚካኤል ሞገስ ስምምነቱ የበጎነት ማሳያ፣ ሀገርና ሕዝብን ያስቀደመ ታሪካዊ ውሳኔ ነው ብለዋል።
በነበረው ግጭት ወጥቶ ለመግባትና ሰርቶ ለመብላት አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞ መቆየቱን አስታውሰው፤ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በየመድረኮችና በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር በተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረብ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር ተናግረዋል።
ፍላጎታቸው ትናንት የተደረሰውን የሰላም ስምንነት እንዲመጣ መሆኑን አውስተው፤ ስምምነቱ እፎይታና ደስታ እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።
ሌላው የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪና የሀይማኖት አባት ሸክ አሕመድ ኑርዬ፤ ስምምነቱ በሀይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በመላ ሕዝቡ በጉጉት ሲጠበቅ የነበር ነው ብለዋል።
ስምምነቱ ለሕዝብ ብስራት፣ ለችግሮች ቁልፍ መፍቻ መንገድ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ የክልሉን እድገትና ብልፅግና ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የግጭትን ዳፋ አይተነዋል ብዙ ኪሳራም አድርሷል፣ መጥፎ ጠባሳም ጥሎ የሚያልፍ ነው ያሉት ደግሞ ፓስተር ዳኘ አዲስ ናቸው።
በግጭቱ በሰዎች ላይ፣ በትምህርት እና በሌሎችም ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰው፤ ከዚህ በኋላ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱበት፣ አርሶ አደሮችም ሆኑ ሰራተኞች በሰላም ወጥተው የሚገቡበት በመሆኑ የሰላም ስምምነቱ ሁሉንም አትራፊና አሸናፊ አድርጓል ብለዋል።
የተደረሰው የዘላቂ ሰላም ስምምነት የበጎነት ማሳያ እና የህዝብ ችግር እንዲያበቃ ተግባራዊ ምላሽ የተሰጠበት፣ ለሕዝብ እፎይታ የሰጠና ሰላምን አፅንቶ ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን የገለጹት የሀይማኖት አባቶቹ፤ ጫካ የቀሩ ወገኖችም የሰላምን መንገደ በመከተል እንዲመጡም የሚያነሳሳ መሆኑን ተናገረዋል።