ቀጥታ፡

በተናበበ የሐሳብና የተግባር አንድነት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንሰራለን - የድሬደዋ አመራሮች

ድሬዳዋ ፤ ህዳር 26/2018(ኢዜአ)፦ በተናበበ የሐሳብና የተግባር አንድነት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆናቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች ተናገሩ።

የመደመር መንግሥት ዋነኛ ግብ የሆነው ታሪክን በመሥራት ውጤትን በተግባር የመግለጥ እሳቤ፤ ህብረተሰቡን በልማት በማሳተፍና ከልማቱ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል፡፡

ሁሉን አቀፍ የልማት ተሳትፎን በአዲስ እይታ በመምራት ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑም ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአመራሮች ስልጠና ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የመደመር መንግስትን እሳቤ ባስረዱበት ወቅት ብልፅግና የሚረጋግጠው አመራሩ ስራን በመፍጠን፣ በመፍጠር፣ በማባዛትና በማጥራት ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ሲችል መሆኑን አስምረውበታል።

ይህ ስልጠናም በየደረጃው እየተሰጠ ሲሆን የድሬደዋ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የመደመር መንግስት እሳቤን ለማሳካት በከፍተኛ ተነሳሽነት እንደሚሰሩ ለኢዜአ ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት አመራሮች የተሰጣቸው ስልጠናዎች ሀገራዊና ክልላዊ የልማት እቅዶችን በቁጭትና በላቀ ተነሳሽነት በመፈጸምና በማስፈጸም የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲተጉ አድርጓቸዋል።


 

የአስተዳደሩ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሌሊሴ አህመድ እንደተናገሩት፤ ሰሞኑን የተሰጠው ሀገራዊ ስልጠና አመራሩ የሃሳብ እና የተግባር አንድነቱን አፅንቶ የህዝብን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንዲሰራ መነሳሳት ፈጥሯል።

የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብም አመራሩ ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ ሌት ተቀን በመስራት ወረትን ለመጪው ትውልድ ለማውረስ መትጋት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡበከር አዶሽ በበኩላቸው ስልጠናው በከፍተኛና መካከለኛው አመራሩ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃት እና ቁጭት መፍጠሩን አንስተዋል።

በተለይም በሁሉም የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ መስኮች የተቀመጡትን ውጥኖች በላቀ ቁርጠኝነት ዳር በማድረስ በየደረጃው የሚገኘውን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ ነው።

የድሬዳዋን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ፀጋዎች ወደ ውጤት ለመቀየር ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስቀመጡት ሀገራዊ የመደመር መንግሥት አቅጣጫዎች መነሻና መዳረሻ ግቦቻችንን በአግባቡ በመረዳትና በተናበበ የተግባር አንድነት ኃላፊነታችንን እንድንወጣ መደላድል ፈጥሯል ያሉት ደግሞ አቶ ሀብታሙ አሰፋ ናቸው።

የህዳሴ ግድብ የድሬደዋ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አሰፋ፤ ድሬዳዋ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉትን ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት መዳረሻ ለማድረግ የተጀመረው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ለማሳካት ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሰይፉ ታደሰ(ዶ/ር) በበኩላቸው ሰሞኑን ለአመራሩ የተሰጠው ስልጠና የብልጽግናን የሚያረጋግጡ የተጀመሩ ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በቁርጠኝነት ለመተግበር የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም