በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።
ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ስድስቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። 22 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር ያስተናገደው አንድ ግብ ብቻ ነው።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ቡድን ንግድ ባንክ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ19 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሰባት ጨዋታዎች ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር 18 ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በአራት ነጥብ የመጨረሻው 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የ10ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ድሬዳዋ ከተማ እና ቦሌ ክፍለ ከተማን ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ያገናኛል።
ድሬዳዋ ከተማ እስከ አሁን በሊጉ ባካሄዳቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ በአምስቱ ተሸንፏል። በጨዋታዎቹ ላይ 10 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ 14 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ12 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ያሸነፈው ቦሌ ክፍለ ከተማ በሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 10 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በተመሳሳይ 10 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቦሌ ክፍለ ከተማ በ13 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።