ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 26/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 9 ሰዓት ወላይታ ድቻ ከምድረገነት ሽሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ወላይታ ድቻ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በስድስት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ተጋጣሚው ምድረገነት ሽሬ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናው በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል። ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አምስት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ምድረገነት ሽሬ በ12 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። 


 

በሌላኛው መርሃ ግብር ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀኑ 10 በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ አራት ጎሎችን አስተናግዷል። 

መድን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በስምንት ነጥብ 15 ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ በሁለቱ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን አስተናግዷል። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ15 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት እስከ ሕዳር 28 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ሲዳማ ቡና ሊጉን በ19 ነጥብ ይመራል። ወላይታ ድቻ፣ መቀሌ 70 እንደርታ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ17ኛ እስከ 20ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም