የሰላም ስምምነቱ በሃሳብ ልእልና ተወያይቶ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ማሳያ ነው - የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱ በሃሳብ ልእልና ተወያይቶ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ማሳያ ነው - የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች
ጎንደር፤ ሕዳር 26/2018(ኢዜአ)፡- የሰላም ስምምነቱ በሃሳብ ልዕልና ተወያይቶ ችግሮችን በሰለጠነና ዘላቂነት ባለው መንገድ መፍታት እንደሚቻል ታላቅ ማሳያ ነው ሲሉ የጎንደር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ኢዜአ በጎንደር ከተማ ያነጋገራቸው የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ፤ በግጭቱ በሰዎች ላይ፣ ከትምህርት ተቋማት ጀምሮ በሌሎችም ተቋማት ላይ ብዙ ኪሳራና ውድመት የደረሰ ስለመሆኑ አስታውሰው፣ ከዚህ ጥፋት ጉዳት እንጂ ትርፍ አለመኖሩን ሁሉም አይቶታል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በኋላ ግን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱበት፣ አርሶ አደሮችም ሆኑ ሰራተኞች በሰላም ወጥተው የሚገቡበት በመሆኑ የሰላም ስምምነቱ ሁሉንም አትራፊና አሸናፊ ማድረጉን ገልጸዋል።
የከተማው የሀገር ሽማግሌ አቶ ወልዴ መና እንደገለጹት፤ የሰላም ስምምነቱ የክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥና ግጭቱ ያስከተለው ጉዳት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲያገኝ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ነው።፡
ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በሃሳብ ልዕልና ተወያይቶ መፍታት ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ህዝቡ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ውስጥ ተፈጥሮ የቆየው ግጭት በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ማስከተሉን አንስተው፤ የሰላም ስምምነቱ የሕዝቡን ተደጋጋሚ የሰላም ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አዲሰ ተስፋን የፈነጠቀ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ሕዝቡ በጉጉት ሲጠብቀው የቆየና በተለያዩ መድረኮችም ሲያነሳቸው ለነበሩ የሰላም ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ የሰጠ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የሀገር ሽማግሌ አቶ አድማሴ ደሞዝ ናቸው፡፡
የሰላም ጥረቱን እንዲሳካ የሰላም ካውንስል አባል በመሆን ታጥቀው ጫካ የገቡ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ የሰላም ስምምነቱ የክልሉ መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ መንግስትና አፋህድ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለሕዝባችን ትልቅ የምስራች ነው ያሉት ደግሞ ቄስ እምሩ መላኩ ናቸው፡፡
ሰላሙ እንዲጸና የሃይማኖት አባቶች አጥብቀን እንጸልያለን ብለዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ በብዙ አካባቢዎች ዋጋ መክፈሉን እና ለችግር መዳረጉን አስተያየት ሰጪዎቹ አስታውሰው ፤ በክልሉ መንግስትና አፋህድ መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት በመፈረሙ የሁላችንም ደስታና ብስራት የተሰማበት ታሪካዊ ዕለት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የችግሮች ሁሉ መቋጫው በውይይትና መግባባት ሰላም መፍጠር መሆኑን አንስተው፤ ለሰላም ቁርጠኛ አቋም ይዘው ለሰሩት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል ዘላቂ የሰላም ስምምነት በትናንትናው ዕለት መፈረሙ ይታወቃል፡፡
የሰላም ስምምነቱን የፈረሙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን በመወከል ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ናቸው።