ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የሀገርን እድገትና ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ ናቸው

ዲላ፤ ህዳር 26/2018 (ኢዜአ) ፡-በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የሀገርን እድገትና ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለስኬት መብቃቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉባ ላይ ባደረጉት ንግግር በድምሩ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተለያዩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ አብስረዋል።

የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኒዩክሌር ኃይል፣ የግዙፍና ዘመናዊ ኤርፖርት ግንባታን ጨምሮ ሌሎችንም የጠቀሱ ሲሆን በዚሁ መሰረት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቷል።

በፕሮጀክቶቹ ላይ ኢዜአ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ያነጋገራቸው ምሁራን እንዳሉት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በድህነት ምክንያት የደረሱ ስብራቶችን በመጠገን የሀገርን እድገትና ማንሰራራት የሚያስቀጥሉ ናቸው።

በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ ዳንኤል ማጻና (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች አሁናዊ ውጤታቸው በብዙ መልኩ እየተገለጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችም የሀገር እድገትና የዜጎች ተጠቃሚነት እውን እየሆነ እንደሚቀጥል አንስተው ፕሮጀክቶቹ ደግሞ እመርታዊ ለውጥ እንደሚያመጡ አንስተዋል። 

የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃት በብዙ ፈተና ውስጥ የተሳካ ድል መሆኑን ዳንኤል (ዶ/ር) አስታውሰው፣ በግድቡ ለተገኘው ድል የመንግስት ጥረትና የመፈፀም አቅምን አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በድህነት ምክንያት የደረሱ ስብራቶችን በመጠገን የሀገርን እድገትና ማንሰራራት የሚያስቀጥሉ ስለመሆናቸውም አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የትምህርትና ሥነ ባህሪ ተቋም ምክትል ዲን ስዩም ጋሪ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የግዙፍ ፕሮጀከቶቹ ግንባታ በቀጣይ የኢትዮጵያን እጣ ፋንታ የሚወስኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ለግብርናው ዘርፍ ማንሰራራት መሰረት ሊሆን ከሚችለው የማዳበሪያ ፋብሪካ ጀምሮ ሌሎቹም ፕሮጀክቶች በሀገር እድገት ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የልማት ፕሮጀከቶቹ  የሀገርን እድገት የሚያፋጥኑ ናቸው ያሉት ደግሞ  በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ገመቹ ኦላኒ ናቸው።

በመሆኑም ለፕሮጀክቶቹ ስኬታማነት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጽናትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ከመገንባት ባለፈ የተጀመረውን የልማት ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራኑ አመላክተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለከፍተኛ አመራሮች በሰጡት ስልጠና የመደመራዊ የዝላይ መንገድ ዋና ዋና ዓላማዎች ከቀዳሚው ጋር ያለ ልዩነትን በፍጥነት ማጥበብ እና እመርታዊ እድገትን ማምጣት መሆኑን ማስረዳታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም