ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለአደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅምና ዝግጁነት እየተፈጠረ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ ሕዳር 26/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለአደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅምና ዝግጁነት እየተፈጠረ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት ስልጠና እና የስራ አቅጣጫ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነት ዜሮ የማድረግ ግብ ማሳካት እንደሚገባ አፅኖት ሰጥተዋል።

በዚህም መሰረት በተለይም ክልሎች ለተፈጥሮና ሰውሰራሽ ችግሮች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም የመገንባት ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ኢዜአ በክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ዩኒት አስተባባሪ አቶ ዳንኤል ታምሩን አነጋግሯል። 

በማብራሪያቸው በክልሉ በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡና እና ሌሎችም የግብርና ዘርፎች እምቅ የመልማት አቅም መኖሩን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ምርታማነትን በማሳደግ በዘላቂነት ከተረጅነት የመውጣትና በአደጋ ጊዜ አስቸኳይ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በበልግ ወቅት ብቻ 29 ሺህ 345 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ያስታወሱት ኃላፊው የመጠባበቂያ ፈንድም በባንክ ስለመቆጠቡ አንስተዋል።

በህዝብና መንግስት ትብብር የመጠባበቂያ ፈንድ ቁጠባ ተጠናክሮ ቀጥሎ በ2018 በጀት አመት ሶስት ወራት ብቻ ከ117 ሚልዮን ብር በላይ ስለመቆጠቡ ጠቁመዋል።

በአይነትና በምርት አሰባሰብ በወላይታ ሶዶ፣ ሳውላ፣ አርባ ምንጭ እና ጂንካ በሚገኙ መጋዘኖች የእህል ክምችት ስለመኖሩ አረጋግጠው በዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች 127 መጋዝኖች ተዘጋጅተው ስራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በክልሉ የሚከሰቱ ችግሮችን በራስ አቅም ለመሸፈንና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በመንግስትና በህዝብ ትብብር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ የአንድ ግቦች ተብለው ከተቀመጡት መካከል በወረዳ ደረጃ አንድ የምርት ማከማቻ መኖር እንዳለበት መግለፃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም