የሚዲያ ሽልማቱ አፍሪካ በዓለም የመረጃ መድረክ እያደገ የመጣውን ተጽእኖዋን የሚያሳይ ነው - ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ - ኢዜአ አማርኛ
የሚዲያ ሽልማቱ አፍሪካ በዓለም የመረጃ መድረክ እያደገ የመጣውን ተጽእኖዋን የሚያሳይ ነው - ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ የሚዲያ ሽልማት አህጉሪቷ በዓለም የመረጃ መድረክ እያደገ የመጣውን ተጽእኖ ፈጣሪነቷን በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ ገለጹ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማት ዛሬ ማምሻውን በአዲስ አበባ ተከናውኗል።
ሽልማቱ ለአፍሪካ ጋዜጠኝነት፣ ብሮድካስት ሚዲያ፣ ዲጂታል ሚዲያ እና ዘገባዎች እውቅና የሰጠ ነው።
በአፍሪካ ሚዲያ ምህዳርን በመቅረጽ ሚናቸውን የተወጡ ጋዜጠኞች ተሸልመዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ የአፍሪካ የሚዲያ ባለሙያዎች የአፍሪካ ዘገባዎች የአህጉሪቷን ነባራዊ ሁኔታ በሚያንጻበርቅ እና ትክክለኛ መረጃን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ስራዎቹ የአፍሪካን የአይበገሬነት፣ ለውጥ እና ተስፋ ትርክቶች አጉልተው ሊያሳዩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሚዲያ ባለሙያዎቹ የአፍሪካን እድሎች፣ ስኬቶች እና የፈጠራ ስራዎች ለዓለም በዘገባቸው ማሳየት አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ የሚነገሩ ነገሮች አሏት ያሉት ሚኒስትሯ እነዚህን የለውጥ፣ ተስፋ፣ ስኬት እና ተስፋ ተረኮች አፍሪካውያን በግልጽ ሊያጋሩ ይገባል ነው ያሉት።
የሚዲያ ሽልማቱ ከሁነቱ ባለፈ አፍሪካ በዓለም የመረጃ መድረክ እያደገ የመጣውን ተጽእኖዋን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) ለማስተናገድ መመረጧን በንግግራቸው ላይ ያነሱት ሚኒስትሯ ይህም ዓለም በኢትዮጵያ አየር ንብረት ዲፕሎማሲ ሚና ላይ ያለውን እያደገ የመጣ እምነት የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል።
ኮፕ 32 ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያላትን የመሪነት ሚና እና ለዘላቂ ልማት ያላትን ቁርጠኝነትም እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ምርጥ የዜና ዘገባ፣ ምርጥ ቃለ መጠይቅ፣ ምርጥ ዶክመንተሪ፣ ምርጥ ወቅታዊ ፕሮግራም፣ ምርጥ አፍሪካ ተኮር የመዝናኛ ፕሮግራም እና ምርጥ የቪዲዮ ፕሮዳክሽን በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ሽልማት የተሰጠባቸው ዘርፎች ናቸው።
አፍሪካ ተኮር ምርጥ የማህበራዊ ሚዲያ ተንቀሳቃሽ ምስል፣ ምርጥ የወቅታዊ ጉዳይ የማህበራዊ ሚዲያ ተንቀሳቃሽ እና ምርጥ አጭር የማህበራዊ ሚዲያ ተንቀሳቃሽ ምስል የማህበራዊ ሚዲያ ሽልማት የተሰጠባቸው ዘርፎች ናቸው።
የአፍሪካ የሚዲያ ሽልማት የአፍሪካን ድምጾች የማጉላት እና የአፍሪካ ጉዳዮች በአፍሪካውያን ብቻ እንዲነገሩ የማድረግ ግብ ያለው ነው።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ