የመጀመሪያው የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2018(ኢዜአ)፦ የመጀመሪያው የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማት ዛሬ ማምሻውን በአዲስ አበባ ተከናውኗል።
በዕውቅና መርሃ ገብሩ የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትአለም መለሰ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት የኮሙኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ዘርፍ ሚኒስትሮችና ተወካዮች እንዲሁም የሚዲያ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ሽልማቱ ለአፍሪካ ጋዜጠኝነት፣ ብሮድካስት ሚዲያ፣ ዲጂታል ሚዲያ እና ዘገባዎች እውቅና የሰጠ ነው።
በአፍሪካ ሚዲያ ምህዳርን በመቅረጽ ሚናቸውን የተወጡ ጋዜጠኞች ተሸልመዋል።
ምርጥ የዜና ዘገባ፣ ምርጥ ቃለ መጠይቅ፣ ምርጥ ዶክመንተሪ፣ ምርጥ ወቅታዊ ፕሮግራም፣ ምርጥ አፍሪካ ተኮር የመዝናኛ ፕሮግራምና ምርጥ የቪዲዮ ፕሮዳክሽን በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ እና ሽልማት የተሰጠባቸው ዘርፎች ናቸው።
አፍሪካ ተኮር ምርጥ የማህበራዊ ሚዲያ ተንቀሳቃሽ ምስል፣ ምርጥ የወቅታዊ ጉዳይ የማህበራዊ ሚዲያ ተንቀሳቃሽ እና ምርጥ አጭር የማህበራዊ ሚዲያ ተንቀሳቃሽ ምስል የማህበራዊ ሚዲያ ሽልማት የተሰጠባቸው ዘርፎች ናቸው።
ሁሉም እጩዎች 2000 ዶላር ሽልማት ያገኙ ሲሆን በእያንዳንዱ ዘርፍ ያሸነፉ ተወዳዳሪዎች የስድስት ሺህ ዶላር ሽልማት አግኝተዋል።
የምርጦች ምርጥ የይዘት ፈጣሪዎች አሸናፊም "The Golden Alkebulan" የተሰኘ ልዩ በወርቅ የተለበጠ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
በሽልማቱ ላይ ከ40 ሀገራት በላይ የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ከ800 በላይ ስራዎችን ማቅረባቸውን ተገልጿል።
የአፍሪካ ሕብረት ብሮድካስቲንግ፣ የፓትሪስ ሉሙምባ ፋውንዴሽን፣ የክዋሜ ንክሩማህ ፋውንዴሽን፣ የምዋሊሙ ኒዬሬሬ ፋውንዴሽን፣ የኬኔት ካውንዳ ሌጋሲ ፋውንዴሽን፣ የሲሱሉ ፋውንዴሽን ለማኅበራዊ ፍትህ፣ የፒኤልኦ ሉሙምባ ፋውንዴሽንና የሩስያው አር ቲ ሚዲያ የሽልማቱ አጋር ናቸው።