የሰላም ስምምነቱ ሁሉንም አሸናፊ ያደረገ፤ ለአማራ ክልል ሕዝብ የዘላቂ ሰላም ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱ ሁሉንም አሸናፊ ያደረገ፤ ለአማራ ክልል ሕዝብ የዘላቂ ሰላም ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2018(ኢዜአ)፦ የሰላም ስምምነቱ ሁሉንም አሸናፊ ያደረገ፤ ለአማራ ክልል ሕዝብ የዘላቂ ሰላም ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑ ተገለጸ።
ከታሪካዊ ጠላቶች እና ከሌሎችም ጋር በጥቅም ተሳስሮ በክልሉ እና በሀገር ላይ የውክልና ጦርነት ማድረግ ታጋይነት ሳይሆን ባንዳነት ነው ሲሉ በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) በመወከል የተፈራረሙት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ገለጹ፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል ዘላቂ የሰላም ስምምነት ተፈርሟል።
ስምምነቱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን በመወከል ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ በዛሬው ዕለት ፈርመዋል።
የሰላም ስምምነት ሂደቱን ሲያስተባብሩና ሲያደራድሩ የቆዩት የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አመራር አባላት ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ስምምነቱን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ የሰላም ስምምነቱ የተፈረመበት ዕለት ለአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ተኩል ዓመታት የክልሉ ሕዝብ በግጭት አዙሪት ውስጥ መቆየቱን ተናግረው፤ ይህም ህይወት የቀጠፈ፣ በርካታ ህጻናትን ከትምህርት ገበታ ውጭ ያደረገ እና የተለያዩ የመሠረተ ልማት ውድመት ያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተፈረመው የሰላም ስምምነት ሁሉንም ኃይሎች አሸናፊ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የክልሉን ህዝብ የሰላም ጥያቄ በመመለስ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ ከስምምነቱ ተጠቃሚ መሆኑን አንስተው፤ በስምምነቱ ከምንም በላይ የአማራ ችግሮችን በውይይት የመፍታት እሴቶች የታዩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘላቂ ሰላም በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ለማጠናከር መሰረት መሆኑን በመግለጽ፤ ስምምነቱም በክልሉ የሰላም ሁኔታ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ነው ያሉት።
የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን በመወከል ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ በበኩላቸው፤ የሰላም ስምምነቱ ታሪካዊ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለማስከበር የሰላም ስምምነቱን መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ መሆን ባንዳነት ነው ያሉት ካፒቴን ማስረሻ ፤ ኢትዮጵያን በራሷ ልጆች የማተራመስ ዓላማ ያላቸውን የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት ባለመቀበል ወደ ሰላም መጥተናል ብለዋል።
ከታሪካዊ ጠላቶች እና ከሌሎችም ጋር በጥቅም ተሳስረው በክልሉ እና በሀገር ላይ የውክልና ጦርነት ማድረግ ታጋይነት ሳይሆን ባንዳነት ነው ብለዋል፡፡
ህዝቡም ይህን እንደማይቀበል የገለጹት ካፒቴን ማስረሻ፤ የባዕዳንን አጀንዳ ተሸክመው የሚንቀሳቀሱ አካላትም ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመጡ ጠይቀዋል፡፡
መነጋገርና መደራደር ሁሉንም አሸናፊ እንደሚያደርግ በመጥቀስ፥ በግጭት የሚመለስ አንድም ጥያቄ አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡
ሌሎች ኃይሎችም የእነርሱን ትክክለኛ ፈለግ በመከተል ወደ ሰላም መምጣት እንዳለባቸው አንስተዋል።
የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የመረጃ ደህንነት መመሪያ ኃላፊ እና የኮር ስራ አስፈጻሚ መስፍን አባተ በበኩላቸው፤ የሰላም ስምምነቱ የጠላቶች አጀንዳ የተሰበረበት በመሆኑ ታሪካዊ ነው ብለዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ በክልሉ ያሉ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶችን በተጨባጭ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወደ ስምምነቱ ያልገቡ ሌሎች አደረጃጀቶች አሁን ያነገቡት አጀንዳ የአማራ ህዝብን የማይጠቅም መሆኑን ተረድተው ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በባንዳነት ተግባር ዘላቂ የክልሉንና የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ እንደማይቻል ጠቁመው፤ የሰላም ስምምነቱ የሁሉንም ወገኖች ጥያቄ በሚመልስ መልኩ መፈረሙን ተናግረዋል።
መንግስት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠትና ለሰላም በሩን በመክፈት ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።