ጉባኤው በኢትዮጵያ ያለውን የካፒታል ገበያ የፋይናንስ ዕድል ለአፍሪካውያን ማስተዋወቅ ያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጉባኤው በኢትዮጵያ ያለውን የካፒታል ገበያ የፋይናንስ ዕድል ለአፍሪካውያን ማስተዋወቅ ያስቻለ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ)፡- ሁለተኛው ቀጣናዊ የካፒታል ገበያ ጉባኤ በኢትዮጵያ ያለውን የካፒታል ገበያ የፋይናንስ ዕድል ለአፍሪካውያን ማስተዋወቅ ያስቻለ መሆኑን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተህልቁ ገለጹ።
ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የሁለተኛው ቀጣናዊ የካፒታል ገበያ ስብሰባ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተህልቁ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አካታች ፋይናንስ ለጋራ ብልጽግና በሚል መርህ የተመሰረተ ነው።
ሁለተኛው ቀጣናዊ የካፒታል ገበያ ስብሰባም የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን ማድረግ የሚያስችሉ ሀሳቦች የተንጸባረቁበት መሆኑን ገልጸዋል።
ስብሰባው በኢትዮጵያ ያለውን የካፒታል ገበያና ሌሎች የፋይናንስ ዕድሎች ለአፍሪካ ማስተዋወቅ አስችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ለወጣቶች ክፍት እንዲሆን መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ መድረኩ ወጣቶች በዘርፉ መመራመር፣ ማጥናትና ማመንጨት የሚችሉበት ዕምቅ አቅም እንዳላቸው የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት፣ ግብይትን የሚያቀላጥፉ ቴክኖሎጂዎችን በማሟላት ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፤ ይሄውም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአፍሪካ የላቀ የካፒታል ገበያ ካላቸው እንደ ናይጄሪያ ካሉ ሀገራት ልምድ መለዋወጥና በጋራ መማማር የሚያስችል ስብሰባ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም በገበያ ቁጥጥር ቴክኖሎጂ፣ የግብይት ስርዓቱንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሟን በተመለከተ ልምዷን አካፍላለች ብለዋል።