ቀጥታ፡

በመደመር መንግሥት እይታ የክልሉን ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው

ደብረ ብርሃን/ወልዲያ/ደብረ ማርቆስ፤ ህዳር 25/2018(ኢዜአ)፦ በመደመር መንግሥት እይታ የክልሉን ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) ገለፁ።

"በመደመር መንግሥት ዕይታ፥ የዘርፎች ዕመርታ’’ በሚል መሪ ሀሳብ በደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ እና ወልዲያ ከተሞች የመካከለኛ አመራሮች ስልጠና ዛሬ መሰጠት ተጀምሯል።


 

በደብረ ብርሀን ከተማ የስልጠናው መድረክ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት የብዝሀ ዘርፍ እይታ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስችሏል።

ይህን አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉን ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

በተለይ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በዲጂታላይዜሽንና በከተሞች ልማት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል አመራሩን በእውቀትና በክህሎት የማብቃት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።


 

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ በዚሁ መድረክ ላይ እንዳሉት፤ በመደመር መንግሥት እሳቤ የዞኑ ህዝብ በኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጠቃሚነቱን ማሳደግ ተችሏል።

ለአብነትም ባለፉት አራት ወራት ብቻ በዞኑ ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ሁሉን አቀፍ የልማት ፖሊሲዎች እንዲሳኩ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመታገል በቁርጠኝነት መስራቱን በመድረኩ ያነሱት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ናቸው።


 

የህዝብ አገልግሎቶች ቀልጣፋና ፍትሀዊ እንዲሆኑ በቴክኖሎጂ የታገዘ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በመተግበር የመደመር መንግሥት እሳቤን እውን ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

አመራሩ በመደመር መንግሥት እይታ በተቃኘ አስተሳሰብ በመመራት ለከተማችን ዘርፈ ብዙ ልማት ሊተጋ ይገባል ያሉት ደግሞ በወልዲያ ከተማ በተካሄደ የስልጠና መድረክ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የወልዲያ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተስፋዬ ገብሬ ናቸው።

በከተማዋ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት፣ የመልካም አስተዳደርና የጸጥታ ሥራዎች ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው የመደመር መንግሥት ወቅታዊና ተሻጋሪ አጀንዳዎች ናቸው ብለዋል።


 

በመደመር መንግሥት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በሌሎችም ዘርፎች ውጤት ለማስመዝገብ በርብርብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ በተካሄደ የአመራር ስልጠና የተሳተፉት በብልጽግና ፓርቲ የከተማ አስተዳደሩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ መልካሙ ሽባባው አመራሩ በእውቀትና በክህሎት እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

አቅሙን በማሳደግ የመደመር መንግሥት እይታ ዘርፎችን እንዲፈጽምና እንዲያስፈጽም የማድረግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

ስልጠናው በአመራሩ መካከል የሃሳብ አንድነትና መቀራረብን በማጠናከር የብልጽግና እሳቤዎችን በውጤታማነት መፈጸም ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል።

ስልጠናው በመደመር መንግሥት እይታ የግብርና እና የገጠር ትራንስፎርሜሽን፣ የኢንዱስትሪ፣ የከተማ ልማትና የቱሪዝም እመርታዎች ላይ አተኩሮ እየተሰጠ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም