በየደረጃው ያለ አመራር በላቀ ዝግጁነትና የተደመረ አቅም ለልማት መትጋት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በየደረጃው ያለ አመራር በላቀ ዝግጁነትና የተደመረ አቅም ለልማት መትጋት አለበት
ባሕር ዳር፣ ሰቆጣና ደሴ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ)፡-በየደረጃው ያለ አመራር በላቀ ዝግጁነትና የተደመረ አቅም ለልማት መትጋት አለበት ሲሉ የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።
‘’በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እምርታ’’ በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳር፣ ሰቆጣ እና ደሴ ከተሞች የመካከለኛ አመራሮች ስልጠና መካሄድ ጀምሯል።
በባህር ዳር ከተማ በተጀመረው ስልጠና ላይ ንግግር ያደረጉት የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፤ የተጀመረውን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሳካት በተለይም የአመራሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማው ሰላምን ከማፅናት ጎን ለጎን በልማት ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በየደረጃው ያለ አመራር በላቀ ዝግጁነትና የተደመረ አቅም ለልማት መትጋት አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል።
በሰቆጣ በተጀመረው መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት በብልፅግና ፓርቲ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳግም ባይነሳኝ፤ በለውጡ ዓመታት በሁሉም ዘርፎች በተጨባጭ እድገትና ማንሰራራት ስለመምጣቱ አንስተዋል።
በዚህ ሂደት የአመራሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተው የብዝሃ ዘርፍን ያማከለውን ስትራቴጂ በፍጥነትና በጥራት በመፈፀምና በማስፈፀም ለላቀ ስኬት መትጋት እነደሚገባ አስገንዝበዋል።
በደሴ ከተማ በተጀመረው መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተስፋ ዳኛው፤ የመፍጠርና የመፍጠን ባህልን በማጎልበት እና ሀብትን በማልማት ለህዝብ ተጠቃሚነት መስራት አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል።
በባህር ዳር መድረክ የተሳተፉት የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን በበኩላቸው እንደገለጹት ብልፅግና ፓርቲ ሁሉንም ፕሮግራሞች በአግባቡ የተገነዘበ አመራር የመገንባት ሥራ ባልተቋረጠ ሁኔታ እያከናወነ ይገኛል።
ያለግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ማዕድን ልማትና ዕድገትን ማረጋገጥ እንደማይቻል ጠቅሰው አመራሩ በየዘርፉ ያሉትን የልማት ዕቅዶች በውል ተረድቶ ለውጤታማነቱ መትጋት እንዳለበት አክለዋል።
ዛሬ ለመካከለኛ አመራሮች መሰጠት የተጀመረው ስልጠና እስከ ታህሳስ 2 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን የተለያዩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመላክቷል።