የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር ከቫይረሱ ራስን መጠበቅ ይገባል - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር ከቫይረሱ ራስን መጠበቅ ይገባል - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2018(ኢዜአ)፡- የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በአግባቡ በመተግበር ራስን ከማርበርግ ቫይረስ መጠበቅ እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር አስገነዘበ።
የጤና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር አስቻለው ወርቁ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የማርበርግ ቫይረስ ህመም የሚከሰተው በቫይረስ ምክንያት ነው።
በአብዛኛው ከታካሚው በሚወጡ የሰውነት ፈሳሾች እንዲሁም በአካላዊ ንክኪ ህመሙ ካለበት ሰው እንደሚተላለፍም አስረድተዋል።
ስለዚህ አካላዊ ንክኪ አለማድረግ፣ የዕጅ ንጽህናን መጠበቅ (በውኃና በሳሙና መታጠብ ወይም ሳኒታይዘር መጠቀም) ከመከላከያ ዘዴዎቹ መካከል መሆኑን አስገንዝበዋል።
የዕጅ ንጽህናን ሳይጠብቁ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን መንካት እንደማይገባም ተናግረዋል።
የህመም ስሜት ሲኖርም በአቅራቢያ ወደሚገኝ የሕክምና ተቋም በፍጥነት መሄድ(በአቅራቢው ላለ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ድንገተኛ ምላሽ ቡድን በማሳወቅ ቀጣይ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
አካላዊ ንክኪ እንዲኖርና ህመሙ እንዲተላለፍ ከሚያስችሉ ሁኔታዎች ራስን መቆጠብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰዎች በብዛት በሚሰባሰቡባቸው የትራንስፖርት፣ የሐይማኖት እና የሥራ ከባቢዎች አካላዊ ንክኪ ሳይኖር አገልግሎት መስጠት ብሎም ማግኘት እንደሚገባ መክረዋል።
ከላይ የተገለጹትን ጥንቃቄዎች በአግባቡ መተግበር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ብሎም በቫይረሱ አለመያዝን ከፍ ማድረግ እንደሚያስችል አመላክተዋል።