ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ባህልን ለማስተዋወቅና የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እያገዘ ነው

ሮቤ፤ህዳር 25/2018 (ኢዜአ)፡-የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ባህልን ከማስተዋወቅ ባለፈ የእርስ በርስ ግንኙነትን እያጠናከረ መምጣቱን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ። 

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አባላት 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብረዋል።


 

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በልዩነታቸው ውስጥ በአብሮነት እንደሚኖሩ የሚያሳዩበት ነው ብለዋል። 

በዓሉ የህዝቦችን አብሮነትና የቆየ ትስስር ከማጎልበት ባለፈ ባህልና እሴቶቻቸውን በማስተዋወቅ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ትምህርት መምህር ኢብራሂም ሐጅ ኡስማን በበኩላቸው የቀኑ መከበር ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲኖራቸው ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አመልክተዋል። 

በተለይ የግጭት ምንጭ የሚሆኑ ከፋፋይ ትርክቶችን በማስቀረት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እንዲጎለብት የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት። 

"ኢትዮጵያ ብዝኃ ማንነት፣ ባህልና ታሪክ ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች ተዋደውና ተቻችለው በፍቅር የሚኖሩባት ሕብረ-ብሔራዊ አገር ናት" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ካሚል ከድር ናቸው። 

የብዝኃ ማንነት፣ ባህል፣ ታሪክ ባለቤት በሆነች አገር በመደመር እሳቤ ተሰናስለው በአንድነት መኖር አማራጭ የለውም ብለዋል። 

ቀኑ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲከበር መደረጉ ተማሪዎች የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ እንዲረዱ ዕድል ይሰጣል ሲሉም ተናግሯል። 

በበዓሉ ከታደሙ ተማሪዎች መካከል የ5ኛ ዓመት የህግ ተማሪ ሀዊ ፍቃዱ በሰጠችው አስተያየት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ባህልና እሴቶችን ለማስተዋወቅ ካለው ፋይዳ ባለፈ የእርስ በርስ ግንኙነትታቸውን እያጠናከረ ነው። 

ዩኒቨርሲቲ ከአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ተማሪዎች በአብሮነት የሚኖሩበትና ባህላቸውን የሚለዋወጡበት ነው በማለት ገልጻለች። 

ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ ተማሪ ኛዳክ አይዳክ በበኩሏ ባለፉት ሦስት ዓመታት በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ማክበሯን ተናግራለች። 


 

ዛሬም ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች ባህልና እሴታቸውን በመለዋወጥ በአብሮነት ማክበራቸውን ገልጻ፣ ይህም ሕብረ ብሔራዊ እንድነትን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው ብላለች። 

የዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተማሪ ኮኬት ድሪባ በበኩሏ በዓሉ በብዝሃነት ውስጥ አንድነት የሚደምቅበትና የጋራ እሴቶችም የሚጠናከሩበት ነው ብላለች። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም