ቀጥታ፡

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል ዘላቂ የሰላም ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2018(ኢዜአ)፦ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል ዘላቂ የሰላም ስምምነት ተፈርሟል።

ስምምነቱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ተወካይ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ፈርመዋል።

በስምምነት ስነ ስርአቱ ላይ ልዩነቱ በስምምነት እንዲቋጭ ሲያደራድሩ የቆዩት የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አመራር አባላት ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በግጭት አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርም፤ ከሰላም ግን ሁሉም አሸናፊ ይሆናል።

ልዩነቶችን በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ረፍዶ አያውቅም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዛሬ ከረጅም ጊዜ በኋላ ስምምነት መፈረሙ ለህዝቡ ትልቅ እፎይታ ነው ብለዋል።

ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

ስምምነቱ አሁንም ልዩነቶችን በሃይል መፍታት ይቻላል የሚል አቋም ለያዙ አካላት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል።

ወደ ሰላም አማራጭ መጥተው ልዩነቶችን በሰላም ለመፍታት ፍላጎት ላላቸው አካላት የክልሉ መንግሥት በሩ ክፍት ነው፤ ኑና በጋራ ተወያይተን ለዘላቂ ሰላም እንትጋ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን(አፋሕድ) በመወከል ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ በበኩላቸው፤ ከግጭት ማንም የሚያተርፍ የለም ወደ ሰላም መምጣት ግን ቅድሚያ የሚሰጠው አማራጭ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ህዝባችን ከዚህ በላይ ችግሮችን መሸከም አይችልም ያሉት ካፒቴን ማስረሻ፤ ልዩነቶችን በስምምነት መቋጨት አሸናፊነት ነው ብለዋል።

ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመወገን የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጡ ተግባራት ላይ መሳተፍ እንደማይገባ ያነሱት ካፒቴን ማስረሻ፤ ችግሮችና የሀሳብ ልዩነቶችን በንግግር መፍታት ፖለቲካዊ ሽንፈት ሳይሆን ጥበብና ብልጠት ነው ብለዋል።

በስምምነቱ በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።

በግጭቱ ምክንያት ዜጎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሉት ካፒቴን ማስረሻ፤ ስምምነቱ ትልቅ ውጤት ይዞ ይመጣል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ በበኩላቸው፤ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እና አማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል የተደረገው ስምምነት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህ በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑን አንስተዋል።

የጥይት ደምጽ የማይሰማበት አፍሪካን እውን ለማድረግ የተቀመጡ አህጉራዊ ግቦች እንዲሳኩም መሰል ስምምነቶች ፋይዳቸው ትልቅ መሆኑን አብራርተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን ኢጋድ ምክትል ዋና ጸሃፊ መሐመድ አብዲ ዋሬ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ ሰላም መረጋገጥ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

ልዩነቶችን በንግግር መፍታት ትልቅ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል ያሉት ምክትል ዋና ጸሀፊው ሁለቱም ወገኖች ለስምምነቱ ቁርጠኛ መሆናቸውን አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም