ቀጥታ፡

በከተማው የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው

ደብረ ማርቆስ፤ ህዳር 25/2018 (ኢዜአ) ፡-በደብረ ማርቆስ ከተማ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ  የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ወራት የተከናወኑ የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች አፈፃፀም የግምገማ መድረክ ተካሄዷል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ በወቅቱ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ትኩረት በመስጠት በስፋት እየተከናወኑ ነው።


 

በዚህም ባለፉት ወራት ሰላምን ከማፅናት ጎን ለጎን  ህብረተሰቡን ያሳተፈና ተጠቃሚነቱን ያረጋገጠ የልማት ስራዎችን ማከናወን ተችሏል ሲለ አክለዋል።

በተለይም በንግድ እንቅስቃሴ፣ በገቢ አሰባሰብ፣ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋትና መሰል ተግባራት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ገልፀዋል።

በቀጣይ ጊዜያትም  የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ለማሳደግ ሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

በብልጽግና  ፓርቲ የከተማ አስተዳደሩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መልካሙ ሽባባው እንዳሉት፤ ባለፉት ወራት የተከናወኑ የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ስራዎች እምርታዊ ለውጥ ማስመዝገብ የቻሉ ናቸው።

በተለይ ህዝብና መንግስት ተቀራርቦ በበሰለ እና በሰከነ አስተሳሰብ እንዲመክር ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ለሰላምና ለልማት ስራዎችም የራሱን አስተዋጾኦ ማበርከት እንዲችል ተሳትፎውን ማጠናከር የተቻለ መሆኑንም አመልክተዋል።

ቀጣይ ማህበረሰቡ የሰላሙ ባለቤት እና የልማቱ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የዋጋ ግሽበቱን ለመከላከል የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትን የማጠናከር እና የማቋቋም ስራ ተከናውኗል ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ዮሴፍ መለሰ ናቸው።

ሃላፊው አክለውም ያለአግባብ የዋጋ ጭማሬ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል።

የከተማው የገቢዎች መምሪያ ሃላፊ አቶ ጌታቸው አለበል በበኩላቸው፤ በበጀት አመቱ አራት ወራት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ521 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ226 ሚሊየን ብር ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የገቢ አቅምን ለማሳደግ በጋራ ርብርብ የሚጠይቁ ስራዎች ላይ በማተኮር እንደሚሰራ አመላክተዋል ።

በመድረኩ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም