ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን- የሃይማት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን- የሃይማት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች
ጎንደር ፤ ሕዳር 25/2018(ኢዜአ)፡-የፍቅርና የአንድነት መሰረት የሆነውን ሰላምን ለማፅናት በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጎንደር ከተማ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አስታወቁ፡፡
የጎንደር ከተማና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያዘጋጀው የሰላም ጥሪ ሕዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡
በሰልፉ ላይ ከተሳተፉ የሀይማኖት አባቶች መካከል ሃጂ ሃሚድ ሀሰን በወቅቱ እንዳሉት፤ የሁሉም ሃይማኖት ተቋማት አስተምህሮ ሰላምን፣ፍቅርንና አንድነትን መስበክ ነው።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የዓመታት አብሮ በሰላም የመኖር ታሪክ ያላት መሆኗን አንስተው፤ ይህን መልካም እሴት ትውልዱ እንዲያስቀጥለው የሃይማኖት መሪዎች ታላቅ አደራና ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡
በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትና አብሮነት እንዲቀጥል በማድረግ በተለይም ሰላምን በመስበክ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ ቄስ እምሩ መላኩ ናቸው፡፡
የሃይማኖት አባቶች ስለ ሰላም አጥብቀን በማስተማር ችግሮችን በውይይትና በምክክር እንዲፈቱ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ አስታወቀዋል፡፡
አቶ አድማስ ደሞዜ በበኩላቸው፤ አለመግባባቶች በምክክር እልባት አግኝተው ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን በመስበክ ምእመናኑ የሰላምን መንገድ እንዲከተሉ የማድረግ ታላቅ አደራ አለባቸው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ አባል መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ናቸው፡፡
የሕዝቦች ፍቅር ፣አንድነትና አብሮነት ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው የሰላም ጥሪ ዓላማ የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይትና በምክክር ተፈተው ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
የጎንደር ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ስልጣናት ቆሞስ አባ ዮሴፍ ደስታ ፤ በግጭት የተፈታ ችግር ባለመኖሩ በሃሳብ ልዕልናና ሙግት ወደ ሰላም ማዕድ በመምጣት ሰላምን ማፅናት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት የእምነት ልዩነት ሳይገድበን የሰላም አምባሳደር በመሆን በሕብረት የሀገራችን ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል ለሰላም ግንባታ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል፡፡
በከተማው የሰፈነው ሰላም ለልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡
የከተማዋ ልማትን ለማስቀጠል የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም መስፈን ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ችግር ውስጥ የገቡ ወገኖች መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል የበደሉትን ሕዝብ ለመካስ እድሉን ሊጠቀሙበት እንደሚገባም አንስተዋል።
መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሀድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ልማት ገብተው ሕብረተሰቡን እንዲክሱ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡