የአዋጁ መሻሻል የፖለቲካ ፓርቲዎች በ7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችል ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የአዋጁ መሻሻል የፖለቲካ ፓርቲዎች በ7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችል ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ መሻሻል ፓርቲዎች በ7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ የአዋጁን መሻሻል አስመልክቶ ለኢዜአ እንዳሉት ምርጫ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ ቁልፍ ሚና አለው።
የጋራ ምክር ቤቱ 7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ግልፅ፣ ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ እንዲሆን የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ላይ የዕጩዎች ድጋፍ ማሰባሰብን የሚመለከተው አንቀጽ እንዲሻሻል የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል።
የጋራ ምክር ቤቱም ጥያቄውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማቅረቡን አስታውሰዋል።
ይህን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅን በማሻሻል የዕጩዎች ድጋፍ ፊርማ እንዲታገድ መወሰኑን አድንቀዋል።
ውሳኔው በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዙሮች ከተካሄዱ ምርጫዎች የተሻለ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል አሰራር መፍጠርንና በትብብር የመስራት ቁርጠኝነትን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዋጁ መሻሻል የፖለቲካ ፓርቲዎች በ7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችልና ለመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የጋራ ምክር ቤቱ 7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ዲሞክራዊያዊና አሳታፊ እንዲሁም ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ መልኩ እንዲካሄድ ፍኖተ-ካርታ ማዘጋጀቱን ሰብሳቢው አስረድተዋል።
ይህም ምርጫው የተሳካ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ላይ በትብብር እንዲሰሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።