ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የኬንያ እና የኒውዚላንድ አምባሳደሮች አሰናበቱ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የኬንያ እና የኒውዚላንድ አምባሳደሮች አሰናበቱ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ)፡- የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ ኦሪና እና የኒውዚላንድ አምባሳደር ማይክል አፕተንን ዛሬ አሰናብተዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ ሁለቱ አምባሳደሮች በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከሀገራቱ ጋር በሁሉም መስኮች የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር እንዲጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የልማት ትብብር፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የአቅም ግንባታ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲሳለጥ እንዲሁም በሌሎች የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ትብብር እንዲጠናከር ማድረጋቸውንም ፕሬዝዳንቱ አንስተዋል።
ተሰናባች አምሳደሮቹ በአዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እና ሌሎች የትብብር ዘርፎች ሁለቱ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ስለሚኖራቸው ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ባሉበት ሆነው አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
አምባሳደሮቹ በበኩላቸው፥ በቆይታቸው ኬንያና ኒውዚላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ማከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት እየጎለበተ መምጣቱን ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
ተሰናባቹ የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ ኦሪና ሀገራቸው ከቀድሞው የኬንያ መሪ ጆሞ ኬንያታ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገች መምጣቷን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ እና ኬንያ ግንኙነት በምስራቅ አፍሪካ በንግድ፣ በመሰረተ ልማት ትስስር፣ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና በጸጥታ ትብብር እየጎለበተ መምጣቱን ጠቁመዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ትብብር በምስራቅ አፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን ነው ብለዋል።
የኒውዚላንድ አምባሳደር ማይክል አፕተን በበኩላቸው በነበራቸው ቆይታ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ በቴክኖሎጂ እና በአቅም ግንባታ ያላትን ትብብር እንድታጠናክር መስራታቸውን ጠቁመዋል።