ምክር ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ እንዲታገድ ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል የአዋጅ ማሻሻያ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ እንዲታገድ ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል የአዋጅ ማሻሻያ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ)፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ እንዲታገድ ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል የአዋጅ ማሻሻያ በማድረግ አጸደቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችንና የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል።
ከጸደቁ ረቂቅ አዋጆች መካከል የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ይገኝበታል። አዋጁን በማሻሻል በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
አዋጁ እንዲሻሻል የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ የሚደነግገው አንቀጽ እንዲታገድ በጋራ ምክር ቤታቸው በኩል በጽሑፍ ማቅረባቸውም ተገልጿል።
የተሻሻለው አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዕጩዎች ምዝገባ ጋር በማያያዝ የሚያሰሙትን ቅሬታ በመፍታትና ጥያቄውን በመመለስ ለሰባተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያስችል ተጠቁሟል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ የማሻሻያ አዋጁን አስመልክቶ ባቀረቡት ማብራሪያ፣ በየደረጃው በሚደረጉ ሁሉን አቀፍ ምርጫዎች በእኩልነትና በነጻነት የማሳተፍ መብትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ጸድቆ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ነው ያስታወሱት።
በዚሁ አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤቶች ለሚያቀርቧቸው እያንዳንዱ ዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲያቀርቡ ተደንግጓል።
ይሁንና የድጋፍ ፊርማ ጥያቄው በስድስተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ወቅት በተከስተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተፈጻሚ እንዳይሆን ታግዶ እንደነበር አፈ ጉባኤው አስታውሰዋል።
የድጋፍ ፊርማ ጥያቄው በሰባተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ተግባራዊ እንዲሆን ማሻሻያ ተደርጎበት የጸደቀ ቢሆንም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቅድመ ዝግጅት ምርጫው እስከ ሚካሄድበት ጊዜ ድረስ የሚሰሩ በርካታ ሥራዎች በመኖራቸውና በቂ ጊዜ ስለሌለ የድጋፍ ፊርማ ለማሰባሰብ እንደሚቸገሩ መግለጻቸውን አንስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ የሚደነግገው አንቀጽ እንዲታገድ በጋራ ምክር ቤታቸው በኩል በጽሑፍ ማቅረባቸውንም አብራርተዋል።
እንደ አፈ-ጉባኤው ማብራሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሰባተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ እንዲሳተፉ አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር የድጋፍ ፊርማውን አስመልክቶ የተቀመጠው አንቀጽ እንዲሻሻል ተደርጓል።
በተሻሻለው አዋጅ መሰረት በሰባተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ አይሰበስቡም ብለዋል።
በአዋጁ አንቀጽ ተቀምጦ የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች ድጋፍ ማሰባሰብ ፊርማ እንዲቀር መደረጉ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለዘላቂ እና ንፁህ የኢነርጂ ተደራሽነት ለውጥን ለማፋጠን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገው የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽደቋል፡፡
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽን እና ቀጣናዊ ውህደት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ተጨማሪ የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅንም አጽድቋል።
በኢትዮጵያና ቻይና መንግሥት መካከል የተደረገውን የወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ስምምነት እንዲሁም ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያና በብራዚል መካከል የተደረገውን ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እና በኢትዮጵያ እና የደቡብ አፍሪካ መንግሥታት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።