ቀጥታ፡

የስደተኞችን መረጃ በአግባቡና በአስተማማኝ ሁኔታ መያዝ የሚያስችሉ የዲጂታል ሥርዓቶች እየተጠናከሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2018(ኢዜአ)፡- የስደተኞችን መረጃ በአግባቡና በአስተማማኝ ሁኔታ መሰብሰብና መያዝ የሚያስችሉ የዲጂታል ሥርዓቶች እየተጠናከሩ መምጣታቸውን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ።

አገልግሎቱ ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር እየተገበረ የሚገኘው የስደት መረጃና ትንተና ሥርዓት ፕሮጀክት ሁለተኛ ምዕራፍ ተጀምሯል።


 

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በወቅቱ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የተለያዩ ሪፎርሞችን በመተግበር የሚሰጠውን አገልግሎት ዘመናዊና ቀልጣፋ እያደረገ ይገኛል።

በተለይ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ማስፋትና ማጠናከር የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር የስደት መረጃና ትንተና ዘመናዊ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ የሚሰጠውን አገልግሎት ተደራሽና ዘመናዊ የማድረግ አንድ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

የስደት መረጃና ትንተና ሥርዓት የመጀመሪያ ምዕራፍ የስደተኞችን መረጃ በአግባቡና በአስተማማኝ ሁኔታ ለመሰብሰብና ለመያዝ እንዲሁም ሌሎች ተግባራትን ለማጠናከር ማስቻሉን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

የስደት መረጃና ትንተና ሥርዓት ሁለተኛው ምዕራፍ አገልግሎቱ ያለውን አቅም ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚያግዘው ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ተወካይ አቢባቱ ዋኔ በበኩላቸው፤ የስደት መረጃና ትንተና ዘመናዊ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ጠቁመዋል።

ትብብሩ በስደት ዙሪያ የተለያዩ ተግባራትን በጋራ ለማከናወን ምቹ መደላድል እየተፈጠረ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የስዊዘርላንድ አምባሳደር ሪካርዳ ቻንዳ በበኩላቸው፤ ስዊዘርላንድ እና ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።


 

በተለይም በስደተኞች ዙሪያ በርካታ ተግባራትን በጋራ እያከናወኑ እንደሚገኙ በመጠቆም፣ በቀጣይም ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም