የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር መደላድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር መደላድል ፈጥሯል
ሀዋሳ፤ ህዳር 25/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር አንድነትን ለማጠናከር መደላድል መፍጠሩ ተገለፀ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ክልላዊ የማጠቃለያ መርሀ ግብር “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሀዋሳ ከተማ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዘሃራ ሁመድ እንዳሉት ቀኑ በአደባባይ መከበሩ የባህል ትውውቅን ለማስፋትና የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር መደላድል የፈጠረ ነው።
ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት ዋስትና የሰጠው የቃል ኪዳን ሰነድ ህገ-መንግስቱ የጸደቀበትን ህዳር 29 ቀን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አውስተዋል።
ቀኑ በህዝቦች አንድነትና ቁርጠኝነት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ያስቻሉ ትልልቅ ልማቶች እየተተገበሩ ባሉበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ናቸው።
በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን በማልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ማስጠበቅ እንደሚገባም አውስተዋል።
በዓሉ የባህል ትውውቅና አብሮነትን ለማዳበር የጎላ ሚና ማበርከቱን የተናገሩት ደግሞ ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ባሻ ገቢሳ ሙለታና ወይዘሮ ዓለም ተስፋዬ ናቸው።