በክልሉ ለሰብዓዊ ድጋፍ እንዲውል በ2 ሺህ 543 ሔክታር ላይ የለማ ሰብል እየተሰበሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለሰብዓዊ ድጋፍ እንዲውል በ2 ሺህ 543 ሔክታር ላይ የለማ ሰብል እየተሰበሰበ ነው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ)፡- ለሰብዓዊ ድጋፍ እንዲውል በዘንድሮው የመኸር ወቅት በ2 ሺህ 543 ሔክታር ላይ የለማ ሰብል እየተሰበሰበ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራርና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ገለጸ።
በ2017/18 የመኸር ወቅት 6 ሺህ 380 ሔክታር በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 543 ሔክታሩን ማልማት መቻሉንና ሰብሉም እየተሰበሰበ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ከዚህም 127 ሺህ 150 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ እና እስካሁንም 14 ሺህ 210 ነጥብ 96 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዓባይነህ አበራ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ካለፈው የበልግ ወቅትም 27 ሺህ 187 ኩንታል ምርት መገኘቱን እና በማከማቻ መቀመጡን ጠቅሰዋል።
በበጋ መስኖ በመኸር ለመዝራት ታቅዶ ያልተፈጸመው አሁን በበጋ መስኖ እንደሚለማ አስረድተዋል።
ከእህል ማከማቻ መጋዘን አንጻር በክልሉ 127 መጋዘኖች መኖራቸውን እና ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ መያዝ የሚችል መጋዘን እየተገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት በበጀት ዓመቱ ባለፉት ወራት ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል 116 ሚሊየን 646 ሺህ 316 ብር መሰብሰቡንም አመላክተዋል።
በአጠቃላይ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ ዐቅም መሸፈን የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዚሁ መሠረት የመንግሥት መዋቅርንና ማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ ጨምሮ በማኅበረሰብ አስቸኳይ ምላሽ በዓይነት እንዲሁም በመንግሥት መጠባበቂያ የመያዝ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ ፈንድ ማቋቋሚያና ማስፈጸሚያ ደንብ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።