ቀጥታ፡

በክልሉ ለችግር የማይበገር እና ዘላቂነት ያለው የጤና ስርዓት የመገንባት ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ባሕር ዳር፤ ሕዳር 25/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ለችግር የማይበገር እና ዘላቂነት ያለው የጤና ስርዓት መገንባት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተመላከተ።

የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአማራ ክልል ከሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎርም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 4ኛው ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) እንዳመለከቱት፤ ለችግሮች የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት ጥራቱን የጠበቀና የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምርምሮችን ማጠናከር ያስፈልጋል።

ለዚህም የክልሉ መንግስት ለችግር የማይበገር እና ዘላቂነት ያለው የጤና ስርዓት መገንባት የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ይህንን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እያደረጉ ያለውን የምርምርና ጥናት ስራዎችን አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ አንስተዋል።


 

የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ ምርምሮችን በማከናወንና በማስተባበር ለፖሊሲ ግብዓትነት እንዲቀርቡ እያደረገ ነው።

በዚህም በክልሉ ከሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጋር በመተባበር አበረታች ስራዎችን ማከናወን እንደተቻለም ጠቅሰዋል።

የጉባኤው ዓላማ የምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበትና በቀጣይም በትብብር የሚሰሩ የምርምር ስራዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥሉ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።


 

በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢና የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አበበ ግርማ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በጤናው ዘርፍ ከኮሮና መከሰት ጀምሮ እስካሁን ወቅታዊና ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጡና የቀውስ ወቅት ምላሽ የምርምር ስራዎችን ከመንግስት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የማከናወን ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲዎች ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም