በዞኑ ሰላምን የማፅናቱ ተግባር ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ኃላፊነታችንን እንወጣለን- አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ሰላምን የማፅናቱ ተግባር ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ኃላፊነታችንን እንወጣለን- አመራሮች
ገንዳ ውኃ ፣ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ):- በምዕራብ ጎንደር ዞን የሰፈነውን ሰላም የማፅናቱ ተግባር ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በዞኑ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ገለጹ።
በዞኑ ባለፉት 5 ወራት የተከናወኑ የሰላምና የልማት ተግባራት አፈጻጸም የግምገማና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የመከረ መድረክ ዛሬ በገንዳ ውኃ ከተማ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ ከዞን፣ ወረዳና ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ አመራሮች ተሳትፈዋል።
ከተሳታፊዎቹ ውስጥ የመተማ ወረዳ አስተዳዳሪ ግዛት ሰረፀ፤ የወረዳው የፀጥታ ሃይል ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ የሕግ የበላይነትን አስከብሮ ሰላምን በማሰፈን ለልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
በወረዳው የሰፈነውን ሰላም በዘላቂነት በማፅናት የልማት ተግባራትን ለማፋጠን ሕብረተሰቡን አስተባብረው በግንባር ቀደምትነት ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የቱሪዝም መስህቦችን የማስተዋወቅ ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የመስኖ ልማት፣ ግብርና እና የመሰረተ ልማት ተግባራት እንደሚጠናከሩም አመላክተዋል።
የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሀብቴ አዲሱ በበኩላቸው፤ የከተማዋን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላምን ማፅናትና ልማትን ማፋጠን ላይ ትኩረት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ከሰላም ማፅናቱ ጎን በጎን የገቢ አሰባሰብን በማጠናከር የሕዝቡን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተናበበ እና በተቀናጀ መንገድ ይሰራልም ብለዋል።
የሕግ የበላይነትን በማስከበር የወረዳውን ሰላም ለማስጠበቅ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ አቀናጅተው አበክረው እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ የቋራ ወረዳ አስተዳዳሪ አስማረ አንዳርጋቸው ናቸው።
የሌማት ትሩፋት፣ የቱሪዝም ዘርፍን ማስፋፋት፣ የመስኖ ልማትን ጨምሮ ሌሎችንም የልማት ተግባራት በገጠር ቀበሌዎች ጭምር ተደራሽ በማድረግ ግንባር ቀደም ሆነው ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ በበኩላቸው፤ ሰላምን በማፅናት የልማት ተግባራትን በውጤታማነት ይበልጥ ለማጠናከር አመራሩ በግንባር ቀደምትነት ትጋቱን ማላቅ እንዳለበት ተናግረዋል።
ሁሉም የዞንና የወረዳ አመራሮች እስከ ታችኛው ቀበሌ ድረስ በመውረድ በየዘርፉ የሕዝቡን እርካታ ለማረጋገጥ መትጋት አለበት ብለዋል።
ሀገሪቱ የያዘቸውን የብልፅግና ጉዞ በአጭር ጊዜ ለማሳካትም አመራሩ ሕብረተሰቡን በማስተባበር መረባረብ እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል።
በግምገማው መድረክ ላይ የተገኙት በሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሙላው በየነ ፤ በዞኑ የሰላምና የፀጥታ ሥራዎችን ዳር ለማድረስ በሚደረገው ጥረት አመራሩ ተሳትፎውን ይበልጥ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ሰራዊቱ ከአመራሩ፣ ከሕዝቡና ከክልሉ የፀጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም ለማፅናት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።